ዘፀአት 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሙሴ ልደት 1 ከሌዊ ወገን እንበረም የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም ከሌዊ ሴቶች ልጆች ሚስትን አገባ። 2 ሴቲቱም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ በአዩ ጊዜ ሦስት ወር ሸሸጉት። 3 ደግሞም ሊሸሽጉት በአልቻሉ ጊዜ እናቱ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፤ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። 4 እኅቱም ምን እንደሚደርስበት ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትጐበኘው ነበር። 5 የፈርዖንም ሴት ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፤ ደንገጥርዋንም ልካ አስመጣችው። 6 ሣጥኑን በከፈተችም ጊዜ ሕፃኑን አየች፤ እነሆም፥ ሕፃኑ በሣጥኑ ውስጥ ያለቅስ ነበር፤ የፈርዖንም ልጅ አዘነችለት፥ “ይህ ሕፃን ከዕብራውያን ልጆች አንዱ ነው” አለች። 7 የዚያም ሕፃን እኅት ለፈርዖን ልጅ፥ “ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?” አለቻት። 8 የፈርዖንም ልጅ፥ “ሂጂና ጥሪልኝ” አለቻት፤ ብላቴናዪቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች። 9 የፈርዖንም ልጅ፥ “ይህን ሕፃን ተንከባክበሽ አጥቢልኝ፤ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ” አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። 10 ሕፃኑም በአደገ ጊዜ ወደ ፈርዖን ልጅ ወሰደችው፤ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው ። ሙሴ ወደ ምድያም እንደ ሸሸ 11 ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አደገ፤ ወደ ወንድሞቹም ወጣ፤ መከራቸውንም ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው ከወንድሞቹ ከእስራኤል ልጆች አንዱን ዕብራዊ ሰው ሲመታ አየ። 12 ወዲህና ወዲያ ተመለከተ፤ ማንንም አላየም፤ ግብፃዊውንም ገደለው፤ በአሸዋ ውስጥም ቀበረው። 13 በሁለተኛውም ቀን ወጣ፤ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ ሙሴም በዳዩን፥ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። 14 ወንድሙን የሚበድለው ያም ሰው፥ “በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን ትናንት እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን?” አለው። ሙሴም፥ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአልን?” ብሎ ፈራ። 15 ፈርዖንም ይህን ነገር ሰማ፤ ሙሴንም ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፤ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ ወደ ምድያም ምድር በደረሰ ጊዜም በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ። 16 ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የአባታቸውንም የዮቶርን በጎች ይጠብቁ ነበር፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፤ የአባታቸውንም የዮቶርን በጎች ሊያጠጡ የውኃዉን ገንዳ ሞሉ። 17 እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ አዳናቸው፤ እየቀዳም በጎቻቸዉን አጠጣላቸው። 18 ወደ አባታቸውም ወደ ራጉኤል መጡ እርሱም፥ “ዛሬስ እንዴት ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። 19 እነርሱም፥ “አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፤ ደግሞም ቀዳልን፤ በጎቻችንንም አጠጣልን” አሉት። 20 ልጆቹንም፥ “ሰውዬው ወዴት ነው? ለምንስ ያን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት፤ እንጀራም ይብላ” አላቸው። 21 ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። 22 ያችም ሴት ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ ሙሴም፥ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። ዳግመኛም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ ስሙንም ኤልኤዜር አለው፤ የአባቴ ፈጣሪ ረዳቴ ነው ሲል። 23 ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፤ ጮኹም፤ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። 24 እግዚአብሔርም ጩኸታቸውን ሰማ፤ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ዐሰበ። 25 እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች ጐበኛቸው፤ ታወቀላቸውም። |