ኢሳይያስ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በኢየሩሳሌም ስለሚደርስ ሁከት 1 እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ኀይለኛውን ወንድና ኀይለኛዋን ሴት፥ የእንጃራን ኀይል ሁሉ፥ የውኃውንም ኀይል ሁሉ ያስወግዳል፤ 2 ኀያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነቢዩንም፥ ዐዋቂውንም፥ ሽማግሌውንም፥ 3 የአምሳ አለቃውንም፥ የተከበረ አማካሪውንም፥ ጠቢቡንም፥ የአናጢዎቹንም አለቃ፥ አስተዋይ አድማጩንም ያስወግዳል። 4 በእነርሱ ላይ አለቆቻቸው እንዲሆኑ ጐልማሶችን እሾምባቸዋለሁ፤ ዘባቾችም ይገዙአቸዋል። 5 ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ ሰው በሰው ላይ፥ ሰውም በባልንጀራው ላይ ይገፋፋል፤ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ፥ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይታበያል። 6 ሰውም በአባቱ ቤተ ሰብእ ውስጥ ወንድሙን ይዞ፥ “አንተ ልብስ አለህ፥ አለቃም ሁንልን፥ ምግባችንም ከእጅህ በታች ትሁን” ቢለው፥ 7 በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ለሕዝቡ አለቃ አልሆንም” ብሎ መለሰለት። 8 ኢየሩሳሌም ተፈትታለችና፥ ይሁዳም ወድቃለችና፥ አንደበታቸውም ዐመፅን ስለሚናገር ለእግዚአብሔር አልታዘዙም። 9 ዛሬም ክብራቸው ተዋርዷልና፥ ፊታቸውም አፍሯልና ኀጢአታቸው እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ኀጢአት ተቃወመቻቸው፤ በላያቸውም ተገልጣ ታወቀች። 10 ክፉ ምክርን መክረዋልና ለነፍሳቸው ወዮላት! እንዲህም አሉ፥ “ጻድቁን እንሻረው፤ ሸክም ሆኖብናልና፤” ስለዚህ የእጃቸውን ሥራ ፍሬ ይበላሉ። 11 እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ይደርስበታል። 12 ሕዝቤ ሆይ፥ ገዥዎቻችሁ ያስጨንቁአችኋል፤ አስጨናቂዎች ሴቶችም በላያችሁ ይሠለጥኑባችኋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የሚያመሰግኑአችሁ ያስቱአችኋል፤ የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ እንደሚፈርድ 13 ነገር ግን እግዚአብሔር ዛሬ ለፍርድ ይነሣል፤ በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ይነሣል። 14 እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ለፍርድ ይመጣል፤ እንዲህም ይላል፥ “ወይኔን አቃጥላችኋል፤ ከድሃው የበዘበዛችሁትም በቤታችሁ አለ፤ 15 ሕዝቤንስ ለምን ትገፋላችሁ? የድሃውን ፊትስ ለምን ታሳፍሩታላችሁ?” ለኢየሩሳሌም ሴቶች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 16 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፥ “የጽዮን ቆነጃጅት ኰርተዋልና፥ አንገታቸውን እያሰገጉ በዐይናቸውም እያጣቀሱ፥ በእግራቸውም እያረገዱ፥ ልብሳቸውንም እየጐተቱ፥ በእግራቸውም እያማቱ ይሄዳሉና፤ 17 ስለዚህ ጌታ የጽዮን ታላላቅ ሴቶች ልጆችን ያዋርዳቸዋል። እግዚአብሔርም በዚያ ቀን ልብሳቸውን ይገልጣል። 18 በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእግር አልቦውን ክብር፥ መርበቡንም፥ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፥ 19 የጆሮ እንጥልጥሉንም፥ አንባሩንም፥ መሸፈኛውንም፥ ቀጸላውንም፥ 20 ሰንሰለቱንም፥ መቀነቱንም፥ የሽቱውንም ዕቃ፥ አሸንክታቡንም፥ 21 የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም፥ 22 የዓመት በዓልንም ልብስ፥ መጐናጸፊያውንም፥ ልግምበገላውንም፥ ከረጢቱንም፥ 23 መስተዋቱንም ከጥሩ በፍታ የተሠራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዐይነ ርግቡንም ያስወግዳል። 24 እንዲህም ይሆናል፤ ስለ ሥራሽ ክፋት በሽቱ ፋንታ ትቢያ ይሁንብሽ፤ በወርቅ መታጠቂያሽም ፋንታ ገመድ ታጠቂ፤ በራስ ወርቅ ቀጸላሽም ፋንታ ቡሃነት ይውጣብሽ፤ በሐር መጐናጸፊያሽ ፋንታ ማቅ ልበሽ። 25 የምትወጂው ትልቁ ልጅሽ በሰይፍ ይወድቃል፤ ኀያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ። 26 የጌጦችሽም ሣጥኖች ያለቅሳሉ፤ ይዋረዳሉም፤ ብቻሽንም ትቀሪያለሽ፤ ከምድርም ጋር ትቀላቀያለሽ።” |