መዝሙር 144 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 አምላኬ ንጉሤ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፥ ስምህንም ለዘለዓለም ዓለም አመሰግናለሁ። 2 በየቀኑ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም ለዘለዓለም ዓለም ምስጋና አቀርባለሁ። 3 እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ ምስጋናውም እጅግ ብዙ ነው፤ ለታላቅነቱም ዳርቻ የለውም። 4 የልጅ ልጆች ሥራህን ያደንቃሉ፥ ኀይልህንም ይናገራሉ፥ 5 የቅድስናህንም ክብር ታላቅነት ይናገራሉ፥ ተአምራትህንም ያስረዳሉ። 6 “ኀይልህ ግሩም ነው” ይላሉ፥ ግርማህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ያስረዳሉ። 7 የቸርነትህን ብዛት መታሰቢያ ይናገራሉ፥ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ። 8 እግዚአብሔር ይቅር ባይና መሓሪ ነው፥ መዐቱ የራቀ፥ ምሕረቱ የበዛ እውነተኛ ነው፤ 9 እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው። ይቅርታውም በሥራው ሁሉ ላይ ነው። 10 አቤቱ፥ ፍጥረትህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ ጻድቃንህም ያመሰግኑሃል። 11 “ለመንግሥትህ ክብር ይገባል” ይላሉ፥ ኀይልህንም ይነጋገራሉ፥ 12 ለሰው ልጆች ኀይልህን የመንግሥትህንም ክብር ታላቅነት ያስታውቁ ዘንድ። 13 መንግሥትህ የዘለዓለም ሁሉ መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው። 14 እግዚአብሔር በቃሉ ሁሉ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፤ እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣቸዋል። 15 የሰው ሁሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ። 16 ቀኝ እጅህን ትዘረጋለህ፤ በሥርዐትህ ለሚኖሩ እንስሳ ሁሉ ታጠግባለህ። 17 እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። 18 እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። 19 ለሚፈሩት ፈቃዳቸውን ያደርጋል፥ ልመናቸውንም ይሰማል፥ ያድናቸዋልም። 20 እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኀጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል። 21 አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ሥጋም ሁሉ ለዘለዓለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ያመሰግናል። |