ሰቈቃወ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ምሕረትን ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 አቤቱ፥ የሆነብንን ዐስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ። 2 ርስታችን ለሌላ፥ ቤቶቻችንም ለእንግዶች ሆኑ። 3 ድሀ-አደጎች ሆነናል፤ አባትም የለንም። እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል። 4 ውኃችንን በገንዘብ ጠጣን፤ እንጨታችን በዋጋ በትከሻችን ይመጣል። 5 ጠላቶቻችን አሳደዱን፤ እኛም ደክመናል፤ ዕረፍትም የለንም። 6 ግብፃውያንና አሦራውያን፥ እንጀራን ያጠግቡን ዘንድ እጃቸውን ሰጡን። 7 አባቶቻችን ኀጢአትን ሠሩ፤ ዛሬም የሉም፤ እኛም በደላቸውን ተሸከምን። 8 ባሪያዎች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸውም የሚታደገን የለም። 9 ከምድረ በዳ ሰይፍ የተነሣ፥ በሕይወታችን እንጀራችንን እናመጣለን። 10 ከራብ የተነሣ ሰውነታችን ጠወለገ፤ ቍርበታችንም እንደ ምድጃ ጠቈረ። 11 በጽዮን ሴቶች፥ በይሁዳ ከተሞችም ደናግል ተዋረዱ። 12 አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ የሽማግሌዎችንም ፊት አላከበሩም። 13 ጐልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፤ ልጆችም በእንጨት ደከሙ። 14 ሽማግሌዎች ከአደባባይ ጠፉ፤ ጐልማሶችም ከበገናቸው ተሻሩ። 15 የልባችን ደስታ ተሽሮአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል። 16 የራሳችን አክሊል ወድቆአል፤ ኀጢአትን ሠርተናልና ወዮልን! 17 ስለዚህ ልባችን ታምሞአል፤ ስለዚህም ነገር ዐይናችን ፈዝዞአል፤ 18 የጽዮን ተራራ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮዎችም ተመላልሰውባታልና። 19 አቤቱ፥ አንተ ለዘለዓለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው። 20 ስለ ምን ለዘለዓለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረዥም ዘመን ትተወናለህ? 21 አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ። 22 ፈጽመህ ጥለኸናልና፤ እጅግም ተቈጥተኸናል። |