ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የሙታንን ትንሣኤ ከአላመንህ ሳይወለዱ ነፍሳት በክረምት ምን ያህል እንደሚነሡ ስማ፤ ቀድሞ እፍ እንዳለባቸው የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱ ላይ ያርፋልና። 2 እንዲሞቱም ቀድሞ በቃሉ ያዛቸዋል። 3 ሥጋቸው ፈርሶ ሳለ እርሱ እንደ ወደደ ይነሣሉ፤ ዳግመኛም ይታደሳሉ። 4 ዳግመኛም ዝናም በሚወርድ ጊዜ ምድርንም በሚአረካት ጊዜ ይነሣሉ፤ ቀድሞም እንደ ተሠራላቸው ይኖራሉ። 5 በደማዊት ነፍስ ሕያዋን የሚሆኑትና በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ፥ ውኃም የሚያስገኛቸው ሁሉ እርሱ አዝዞአልና ተፈጠሩ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃው ላይ ይሰፍፍ ነበርና፤ በመንፈሱና በቃሉም ደማዊት ነፍስ ትሰጣቸዋለች። 6 ሙታን አይነሡም የምትል አንተ ልበ-ዕውር እስኪ ተመልከት፤ በመንፈሱና በቃሉ ያለ አባትና እናት ይፈጠራሉና፤ ጥበብ ካለህስ ሙታን በፈጣሪያቸው በእግዚአብሔር ቃል አይነሡም እንዴት ትላለህ? 7 አንተስ ንስሓ ግባ፤ ወደ እምነትህም ተመለስ፤ በመቃብር ኣመድና ትቢያ የሆኑ ሙታን በእግዚአብሔር ቃል ይነሣሉና። 8 ቀድሞ ቃሉ እንደ ተናገረ ከእግዚአብሔር በተገኘ በይቅርታ ጠል ይነሣሉ፤ ያም ቃል ሁሉን ዞሮ ሙታንን እንደ ወደደ ያስነሣቸዋል። 9 ተነሥተህም በፊቱ እንደምትቆም ዕወቅ፤ እንደ አሳብህም በመቃብር የምትቀር አይምሰልህ። 10 እንዲህ አይደለም፥ በምድር እንደ ሠራኸው ሥራ በጎም ቢሆን፥ ክፉም ቢሆን፥ ተነሥተህ ዋጋህን ትቀበላለህ፤ ይህች የፍዳ ቀን ናትና። 11 በትንሣኤም ጊዜ በሠራኸው ኀጢአትህ ሁሉ ፍዳህን ትቀበላለህ፤ ከሕፃንነትህ ጀምሮ እስከዚያ ጊዜ ድረስ የተጻፈ ዕዳህን ትጨርሳለህ፤ ኀጢአትህንም ትክድ ዘንድ እንደዚህ ዓለም ሥራ በኀጢአትህ የምታመካኘው ምክንያት የለህም። 12 ሐሰተኛ ቃልህን በፊትህ እውነት እንደምታደርገው፥ የተናገርኸው ሐሰቱንም ነገር እውነት እንደምታደርገው፥ በዚያ የምታመካኘው ምክንያት የለህም። 13 እርሷ የሠራኸውን ክፉ ሥራህን ሁሉ የምታውቅብህ ስለሆነ በፈጣሪዋ በእግዚአብሔር ፊትም የምትገልጥብህ ስለ ሆነ የእግዚአብሔር ቃሉ በአንተ አድሮ ይናገርብሃልና። 14 በዚያም ስለ ሠራኸው ኀጢአትህ ታፍራለህ፤ በመልካም ሥራቸው ከሚመሰገኑ ጋር ትመሰገን ዘንድ ነው እንጂ በፍርድ ቀን በመላእክትና በሰዎች ፊት እንዳታፍር ወደዚያ ሳትደርስ በዚህ ንስሓ ለመግባት ፍጠን። 15 ከመላእክት ጋራ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ያለ ኀፍረት ከፈጣሪያቸው ዋጋቸውን ይቀበላሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ ነገር ግን በሥጋህ በሕይወት ሳለህ በጎ ሥራን ካልሠራህ ከጻድቃን ጋር እድል የለህም። 16 ዕውቀት ሳለህ፥ ዋጋና ገብያም ሳለህ አልተዘጋጀህምና፥ ገንዘብም ሳለህ ለተራበው አላጐረስኸውምና የማይረባ ጸጸት ይሆንብሃል። 17 ልብስም ሳለህ የታረዘውን አላለበስኸውምና፥ ሥልጣንም ሳለህ የተበደለውን አላዳንኸውምና። 18 ዕውቀትም ሳለህ ተመልሶ ንስሓ ይገባ ዘንድ፥ ቀድሞ ባለማወቅ የሠራውንም ኀጢአቱን እግዚአብሔር ይቅር ይለው ዘንድ ኃጥኡን ሰው አላስተማርኸውምና፥ ድል መንሣትንም ትችል ዘንድ ኀይል ሳለህ ከሚጣሉህ ከአጋንንት ጋር አልተዋጋህም። 19 ጽናትም ሳለህ በሥጋ ያለ የሕፃንነትህን ኀይል ታደክም ዘንድ በዓለም ያለ ሥጋን ለማስደሰት ያይደለ ለጽድቅ ራስህን ታስገዛ ዘንድ አልጾምህም፤ አልጸለይህምም። 20 በዓለም በአለ ደስታ፥ በጣፋጭ ምግቦችና በማለፊያ መጠጥ አይደለም፤ በቀጭን ልብስም በወርቅና በብር በማጌጥም አይደለም። 21 በከበሩ በሕንደኬ ዕንቍዎች፥ በጳዝዮንና በመረግድ አይደለም፤ ይህ የሚገባ የሰው ጌጥ አይደለም። 22 ለሰውስ ጌጡ ንጽሕና፥ ጥበብና ዕውቅት፥ ያለ መቅናትና ያለ ምቀኝነት፥ ያለ መጠራጠርና ያለ ጠብ በሚገባ መዋደድ ነው። 23 ባልንጀራህን እንደ ራስህ እየወደድህ፥ ክፉ ባደረገብህ ሰውም ክፉ ነገር ሳታደርግ፥ መከራውን ለታገሡ ሰዎች ወደ ተሰጠ ማደሪያም ትገባ ዘንድ፥ ቅድስት ምድርን በትዕግሥትና በዕውቀት፥ በትንሣኤም ጊዜ መንግሥተ ሰማይን ተስፋ በማድረግ ከወረስዋት ሰዎች ጋር ዋጋህን ይሰጥህ ዘንድ ነው። 24 “ከሞትን በኋላ አንነሣም” አትበሉ፤ ይኽን የሚናገሩና የሚያስቡ ሰዎችን በትንሣኤ ጊዜ እንዳይድኑ ዲያብሎስ ተስፋ ያስቈርጣቸዋልና፥ ትንሣኤም በደረሰችባቸው ጊዜ ያውቃሉ፤ ኀጢአታቸውን ያስብባቸው ዘንድ ባለ ማወቅ ኀጢአት የሠሩ ሰዎች በትንሣኤ ጊዜ ፈጽመው ያዝናሉ፤ በዚያች ቀን እንደሚነሡ አላመኑበትምና። 25 ስለዚህም በምድር ላይ እንደ ሠሩት ሥራቸው ክፋት ይወቀሳሉ፤ በሥጋ በአንድነት የሚነሡባትን የካዷትንም ትንሣኤ ያዩአታል። 26 ሥራቸውንም ስላላሳመሩ ያንጊዜ ያለቅሳሉ፤ ቢቻላቸውስ በዚያ የሚያለቅሱ እንዳይሆኑ፥ በዚህ ዓለም ቢያለቅሱ በተሻላቸው ነበር። 27 በዚህ በፈቃዳችን ካላለቀስን፥ በዚያ ያለፈቃዳችን ያስለቅሱናል፤ በዚህ ንስሓን ካላዘጋጀን፥ በዚያ የማይረባና የማይጠቅም ጩኸትንና ልቅሶን እናዘጋጃለን። 28 ከሞት ወደ ሕይወት፥ ከምታልፍ ከዚህች ዓለምም ወደ ላይኝ`ዋ መንግሥተ ሰማይ፥ ከዚች ምድራዊት ብርሃንም ወደ ሰማያዊት ብርሃን ትሸጋገሩ ዘንድ መልካም ሥራን አዘጋጁ። 29 የሙታን ትንሣኤን ከሚያምኑ ሰዎች ጋር በማያልቅ ደስታ በመንግሥተ ሰማይ ደስ ይልህ ዘንድ በምድር ያለች ደስታን እንቢ በላት፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም አሜን። |