በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ።
ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
“የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለዚህ እንደየሥራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንግዲህ ንስሓ ግቡ፤ በኀጢአት እንዳትጠፉ፣ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።
በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?
ማንም እንዲሞት አልሻምና፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ!
አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።
ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤ በደሌንም አልሸሸግሁም፤ ደግሞም “መተላለፌን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ” አልሁ፤ አንተም የኀጢአቴን በደል፣ ይቅር አልህ። ሴላ
ነገር ግን በመጀመሪያ በደማስቆ ለሚኖሩ፣ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላሉት ሁሉ፣ ከዚያም ለአሕዛብ፣ ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ።
ስለዚህ ለሕዝቡ ንገር፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ተመለሱ፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
ልባችሁን እንጂ፣ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ፣ ቍጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ፣ ክፉ ነገር ከማምጣትም የሚታገሥ ነውና።
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።
ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤
“ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ።
ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
“ቀረጥ ሰብሳቢው ግን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ አልፈለገም፤ ነገር ግን ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ ይል ነበር።
ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በርሱ ላይ ጣሉት።
ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።
ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጐደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤
ደግሞም በአእምሯችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣
እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው።
ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤ የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋራ እሆናለሁ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ።
አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ።
የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ።
እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።
የድነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤ አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል።
ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያውጃል።
መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም።
እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።
በበጎ ፈቃድህ ጽዮንን አበልጽጋት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች ሥራ።
የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤ ኰርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው።
በደሌን ፈጽሞ ዕጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ።
የርስቱን ትሩፍ ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? ለዘላለም አትቈጣም፤ ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።
ተመልሰህ ትራራልናለህ፤ ኀጢአታችንን በእግርህ ትረግጣለህ፤ በደላችንንም ሁሉ ወደ ጥልቁ ባሕር ትጥላለህ።
ከሚውጥ ጕድጓድ፣ ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤ እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤ አካሄዴንም አጸና።
ለአምላካችን የሚሆን ውዳሴ፣ አዲስ ዝማሬን በአፌ ላይ አኖረ፤ ብዙዎች ያያሉ፤ ይፈራሉም፤ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።
ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ወንድሙን የሚወድድ በብርሃን ይኖራል፤ በርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም።
ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።
ልጆች ሆይ፤ ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
አባቶች ሆይ፤ ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ። ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
አባቶች ሆይ፤ ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ። ጐበዛዝት ሆይ፤ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣ ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣ እጽፍላችኋለሁ።
ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማንኛውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድድ የአብ ፍቅር በርሱ ዘንድ የለም፤
ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም።
ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።
ልጆች ሆይ፤ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደ ሰማችሁትም የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል፤ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ የመጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ የምናውቀውም በዚህ ነው።
ከእኛ መካከል ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋራ ጸንተው በኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ተለዩ።
እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።
መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና።
መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ።
ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣ በዚያ ጊዜ አላፍርም።
ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም።
እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል።
ነገር ግን የሰዎችን በደል ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይልላችሁም።
እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹም ልባቸውም ወደ እኔ ስለሚመለሱ፣ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም።
ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ።
ስሕተቱን ማን ሊያስተውል ይችላል? ከተሰወረ በደል አንጻኝ።
ባሪያህን ከድፍረት ኀጢአት ጠብቅ፤ እንዳይሠለጥንብኝም ርዳኝ፤ ያን ጊዜ ያለ እንከን እሆናለሁ፤ ከታላቅ በደልም እነጻለሁ።
ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤
እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።
እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል?
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን! እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባሪያ ስሆን፣ በኀጢአተኛ ተፈጥሮዬ ግን ለኀጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።
ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ።
ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና።
“በጠባቡ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይገባሉ።
ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው።
በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣
በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣
በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንመላለስ፣ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።
ይህም ጸጋ በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፣ በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር ያስተምረናል፤
የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ትበረታላችሁ፤ እናንተ ግን ይህን አላደረጋችሁም፤
ይህም ሆኖ እግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።
እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን? እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?” ይላል እግዚአብሔር። “ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።
ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው።
“ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ።
እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ በዚያ አገር ሁሉ ጽኑ ራብ ሆነ፤ ይቸገርም ጀመር።
ስለዚህ ከዚያ አገር ነዋሪዎች አንዱን ተጠጋ፤ ሰውየውም ዐሣማ እንዲቀልብለት ወደ ዕርሻው ላከው።
ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው አልነበረም።
“ልብ በገዛ ጊዜ ግን እንዲህ አለ፤ ‘ስንቱ የአባቴ ሠራተኛ ምግብ ተርፎታል፤ እኔ ግን እዚህ በራብ ልሞት ተቃርቤአለሁ
ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፣ እንዲህ ልበለው፤ አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤
ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቍጠረኝ።’
ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ይህ ሰው ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋራ ይበላል” እያሉ አጕረመረሙ።
ስለዚህም ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። “ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው።
“ልጁም፣ ‘አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው።
“አባቱ ግን ባሮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤
የሠባውንም ፍሪዳ አምጡና ዕረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት፤
ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቷል።’ ከዚያም ይደሰቱ ጀመር።
“በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ በዕርሻ ቦታ ነበረ፤ ከዚያም ተመልሶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ፣ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤
እርሱም ከብላቴኖቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደ ሆነ ጠየቀው።
አገልጋዩም፣ ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በሰላም በጤና ስለ መጣም አባትህ የሠባውን ፍሪዳ ዐርዶለታል’ አለው።
“ታላቅ ወንድሙም ተቈጣ፤ ወደ ቤትም መግባት አልፈለገም፤ አባቱም ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው።
እርሱ ግን መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፤ ‘እነሆ፤ ይህን ያህል ዘመን እንደ ባሪያ አገልግዬሃለሁ፤ ከትእዛዝህም አንዱን እንኳ አላጓደልሁም፤ አንተ ግን ከባልንጀሮቼ ጋራ እንድደሰት አንዲት የፍየል ግልገል እንኳ አልሰጠኸኝም፤
ኢየሱስም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤
ነገር ግን ይህ ልጅህ ንብረትህን ከጋለሞቶች ጋራ አውድሞ ሲመጣ፣ የሠባውን ፍሪዳ ዐረድህለት።’
“አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋራ ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤
ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ ሕያው ሆነ፤ ጠፍቶ ነበር ተገኘ፤ ስለዚህ ደስ ሊለንና ፍሥሓ ልናደርግ ይገባናል።’ ”
እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋራ ሰላም አለን።
የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከርሱ ጋራ ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም!
ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን።
ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቷል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤
ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም።
ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ።
ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ!
ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ።
በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!
ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ።
በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።
በርሱም በኩል አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን።
እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ።
በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች።
እኔም፣ “ጨለማው በርግጥ ይሰውረኛል፤ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል” ብል፣
ጨለማ የአንተን ዐይን አይዝም፤ ሌሊቱም እንደ ቀን ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንም ለአንተ አንድ ናቸውና።
አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ።
ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።
እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐጥንቶቼ ከአንተ አልተደበቁም፤ በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ፣
ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ ተመዘገቡ።
አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው!
ልቍጠራቸው ብል፣ ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር። ተኛሁም ነቃሁም፣ ገና ከአንተው ጋራ ነኝ።
አምላክ ሆይ፤ ክፉዎችን ብትገድላቸው ምናለበት! ደም የተጠማችሁ ሰዎች ሆይ፤ ከእኔ ራቁ!
አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ።
እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤ ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤ ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣ ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣ የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋራ ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን ፈልጉ፤
የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤
በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው።
እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤
እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ።
በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።
እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ።
የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
በርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
ሚስቶች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ ተገቢ በመሆኑ ለባሎቻችሁ ተገዙ።
ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው።
ሐሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን።
እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ።
ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያውጃል።
መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም።
እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።
መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ወደ እናንተ መጣ፤ እናንተ አላመናችሁትም፤ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ግን አመኑት። የሆነውን ካያችሁ በኋላ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም።
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤
ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
ዕውሮችን በማያወቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤ ባልተለመደ ጐዳና እወስዳቸዋለሁ። ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ። ይህን አደርጋለሁ፤ አልተዋቸውም።
እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤
ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል’
እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’
ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤
ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤
መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋራ የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ።
አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
ስለዚህ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ እግዚአብሔርም በእኛ አማካይነት ጥሪውን ያቀርባል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋራ ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን።
እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል።
በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም።
ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው።
በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ካልሆነ በቀር ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም።
“እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና።