የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ፣ ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው። ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። ከርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል። ስለዚህ ይህን እነግራችኋለሁ፤ በጌታም ዐደራ እላለሁ፤ በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ልትመላለሱ አይገባም። እነርሱ ከልባቸው መደንደን የተነሣ ስለማያስተውሉ ልቡናቸው ጨልሟል፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ተለይተዋል። ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ በማይረካ ምኞት፣ በርኩሰት ሁሉ እንዳሻቸው ለመኖር ቅጥ ለሌለው ብልግና ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።
ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋራ እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።
ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏል።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።
በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።
በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣ በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣ በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።
“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤ ሰዎችም መብራት አብርተው ከእንቅብ በታች አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ። እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።
እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤ እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሠኘውን ፈልጉ። ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋራ ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤ በድብቅ የሚሠሩትን ነገር መናገር ራሱ አሳፋሪ ነውና። ብርሃን የበራበት ነገር ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤ ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣ “አንተ የተኛህ ንቃ፤ ከሙታን ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሏል። እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ። በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና። በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ።
ጕልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እርሱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሣሣ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።
ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
“አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”
ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ አንድ ሐሳብ ይስጣችሁ፤ ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።
የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣
ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። የማይወድድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።
ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ ትእዛዞቼን በልብህ ጠብቅ፤ ይህን ብታደርግ፣ ጐተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤ መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል። ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር፤ አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና። ብፁዕ ነው፤ ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው፤ እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና። ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም። በቀኝ እጇ ረዥም ዕድሜ አለ፤ በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች። መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤ ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል። በዕውቀቱ ቀላያት ተከፈሉ፤ ደመናትም ጠልን አንጠበጠቡ። ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ጥበብና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤ እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤ ለነፍስህ ሕይወት፣ ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ። ከዚያም መንገድህን ያለ ሥጋት ትሄዳለህ፤ እግርህም አይሰናከልም፤ ስትተኛ አትፈራም፤ ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል። ድንገተኛን መከራ፣ በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤ እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤ እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል። ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ። አሁን በእጅህ እያለ፣ ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣ በጎረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት። ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤ በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤ በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው። ምንም ጕዳት ሳያደርስብህ፣ ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ። በክፉ ሰው አትቅና፤ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ። እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል። የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤ የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል። እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል። በዚያ ጊዜ ሞገስንና ማስተዋልን፣ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ።
ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ ዕሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሏል። ስለዚህ በሙሉ ልብ፣ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።
እኛ ብርቱዎች የሆንን፣ የደካሞችን ጕድለት መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። ደግሞም፣ “አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋራ ደስ ይበላችሁ” ይላል። እንደ ገናም፣ “አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑት፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወድሱት” ይላል። ኢሳይያስም እንዲሁ፣ “በሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚነግሠው፣ የእሴይ ሥር ይመጣል፤ በርሱም ሕዝቦች ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል። በርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስስላችሁ ነው። ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነት የተሞላችሁ፣ በዕውቀትም ሁሉ የተሞላችሁና አንዱ ሌላውን ለመምከር ችሎታ ያላችሁ መሆናችሁን እኔ ራሴ ርግጠኛ ሆኛለሁ። እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት፣ እንደ ገና አሳስባችሁ ዘንድ በአንዳንድ ጕዳዮች ላይ በድፍረት የጻፍሁላችሁ፣ በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርን በማገልገሌ በክርስቶስ ኢየሱስ እመካለሁ። በተናገርሁትና ባደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር መንፈስ ኀይል፣ በምልክቶችና በታምራት ነበር። በዚህም ሁኔታ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ። እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን ለማነጽ፣ እርሱንም ለመጥቀም ደስ የሚያሠኘውን ነገር ማድረግ ይገባናል።
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደ ያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ።
እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን ሁሉ፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ። ቀድሞ የርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ መጠን፣ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንድትርቁ እለምናችኋለሁ። ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም፣ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን አይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ። ስለ ጌታ ብላችሁ ለምድራዊ ባለሥልጣን ሁሉ ተገዙ፤ የበላይ ባለሥልጣን ስለ ሆነ ለንጉሥ ቢሆን፣ ወይም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣትና በጎ አድራጊዎችን ለማመስገን እርሱ ለሾማቸው ገዦች ታዘዙ፤ ምክንያቱም፣ መልካም በማድረግ የአላዋቂዎችን ከንቱ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እንደ እግዚአብሔር ባሮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት። ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ። እናንተ አገልጋዮች ሆይ፤ ለደጎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን፣ ለክፉዎችም በፍጹም አክብሮት ታዘዙ። ስለ እግዚአብሔር ሲል የግፍ መከራን የሚቀበል ሰው ምስጋናን ያገኛል። በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤
ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል።
እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን በደል ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይልላችሁም።
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁ በገዛ እጃችሁ ሥሩ፤ በጸጥታ ኑሩ፤ በራሳችሁ ጕዳይ ላይ ብቻ አተኵሩ። ይኸውም፣ በዕለት ተለት ኑሯችሁ በውጭ ባሉት ዘንድ እንዲያስከብራችሁና በማንም ሰው ላይ ሸክም እንዳትሆኑ ነው።
የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው። “እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም።” ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።
እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።
“ማንም ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።
ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው።
ይህን የምለው ስለ ቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣ ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብ፣ ባገኝም ሆነ ባጣ፣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ።
“ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላላወቀው ነው። የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችኋት፣ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል የምትለዋ መልእክት ይህች ናትና፤ የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ፤ ለምን ገደለው? ምክንያቱም የርሱ ሥራ ክፉ፣ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበረ ነው። ወንድሞች ሆይ፤ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። ወንድሞቻችንን ስለምንወድድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደ ሆነ በዚህ እናውቃለን፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል። ማንም የዚህ ዓለም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ልቡ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በርሱ ይኖራል? ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ። እኛ ከእውነቱ መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፤ ወዳጆች ሆይ፤ እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ እናየዋለን፤ እርሱን እንደምንመስልም እናውቃለን።
በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን።
ብፁዕ ነው፣ በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፤ ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል።
ዳሩ ግን ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ ምክንያቱም የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነው። ያ ሰው፣ ከጌታ አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ አያስብ፤ እርሱ በሁለት ሐሳብ የተያዘና በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ነው።
ስለዚህ፣ “ሕይወትን የሚወድድ፣ መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣ ምላሱን ከክፉ፣ ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል። ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤
ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው። የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል።
እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
“ሰዎች እንዲያዩላችሁ፣ መልካም ሥራችሁን በፊታቸው ከማድረግ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ከሰማዩ አባታችሁ ዋጋ አታገኙም። መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ፤ መንግሥት፣ ኀይል፣ ክብርም ለዘላለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን። ’ እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን በደል ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይልላችሁም። “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆነ ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። “ግብዞች በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በየጐዳናውና በየምኵራቡ እንደሚያደርጉት፣ አንተም ለድኾች ምጽዋት በምትሰጥበት ጊዜ ይታይልኝ ብለህ ጥሩንባ አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና። “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን? “ማንም ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም። “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሯችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? እስኪ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ለመሆኑ፣ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማን ነው? “ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስኪ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። እናንተ ግን ለድኾች ስትሰጡ፣ ቀኝ እጃችሁ የሚያደርገውን ግራ እጃችሁ አይወቅ፤ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ እነዚህም ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና። ምጽዋታችሁ በስውር ይሁን፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባታችሁም ዋጋችሁን ይከፍላችኋል።
እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች ተዋደዱ። በድንኳኒቱም የሚያገለግሉ ከዚያ ሊበሉ መብት ያላገኙበት መሠዊያ አለን። ሊቀ ካህናቱ ስለ ኀጢአት ስርየት የሚሆነውን የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፤ የእንስሳቱ ሥጋ ግን ከሰፈር ውጭ ይቃጠላል። እንዲሁም ኢየሱስ በራሱ ደም አማካይነት ሕዝቡን ሊቀድስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ። ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ። ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን። ስለዚህ ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ። ደግሞም መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋራ መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሠኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና። ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጕዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው፤ አለዚያ አይበጃችሁም። ለእኛ ደግሞ ጸልዩልን። በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚናፍቅ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን ርግጠኞች ነን። በተለይም ወደ እናንተ በፍጥነት ተመልሼ እንድመጣ ትጸልዩልኝ ዘንድ ዐደራ እላችኋለሁ። እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ፣ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና።
በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ። ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል፤ እነርሱ ዐላፊ ጠፊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ይደክማሉ፤ እኛ ግን ለዘላለም የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት እንደክማለን።
በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ካልሆነ በቀር ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም። “እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በእናንተ መካከል በትጋት የሚሠሩትን፣ በጌታም የበላዮቻችሁና መካሪዎቻችሁ የሆኑትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ ስለ ሥራቸውም በፍቅር እጅግ አክብሯቸው። እርስ በርሳችሁም በሰላም ኑሩ።
የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ሽሽ፤ ጽድቅን፣ እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወትን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ትዕግሥትንና ገርነትን ተከታተል። መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፤ በብዙ ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የመሰከርህለትንና የተጠራህበትን የዘላለም ሕይወት አጥብቀህ ያዝ።
በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤