Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 27 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 27
የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኅኔ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር ለሕይወቴ ዐምባዋ ነው፤ ማንን እፈራለሁ?

2 ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ፣ ክፉዎች ገፍተው በመጡ ጊዜ፣ ጠላቶቼና ባላጋራዎቼ በተነሡብኝ ጊዜ፣ እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ።

3 ሰራዊት ቢከብበኝ እንኳ፣ ልቤ አይፈራም፤ ጦርነት ቢነሣብኝ እንኳ፣ ልበ ሙሉ ነኝ።

4 እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።

5 በመከራ ቀን፣ በድንኳኑ ውስጥ ይሰውረኛልና፤ በተቀደሰ ድንኳኑም ውስጥ ይሸሽገኛል፤ በዐለቱ ላይ ከፍ ያደርገኛል።

6 በዚህ ጊዜ በዙሪያዬ ባሉ ጠላቶቼ ላይ፣ ራሴ ከፍ ከፍ ይላል፤ በድንኳኑም ውስጥ የእልልታ መሥዋዕት እሠዋለሁ፤ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፤ እዘምርለታለሁም።

7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ስማኝ፤ ራራልኝ፤ ስማኝም።

8 “ፊቴን ፈልጉ” ባልህ ጊዜ፤ ልቤ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊትህን እሻለሁ አለች።

9 ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤ ተቈጥተህ አገልጋይህን አታርቀው፤ መቼም ረዳቴ ነህና። አዳኝ አምላኬ ሆይ፤ አትጣለኝ፤ አትተወኝም።

10 አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል።

11 እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤ ስለ ጠላቶቼም፣ በቀና መንገድ ምራኝ።

12 ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ፤ የሐሰት ምስክሮች ተነሥተውብኛልና፣ ዐመፃ የሚረጩ ናቸው።

13 የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ ሙሉ እምነቴ ነው።

14 እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች