Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሐዋርያት ሥራ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በበዓለ ዐምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወረደ

1 የበዓለ ዐምሳ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፣ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር።

2 ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው።

3 የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ።

4 ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር።

5 በዚህ ጊዜ ከሰማይ በታች ካለው ሕዝብ ሁሉ የመጡና እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይሁድ በኢየሩሳሌም ነበሩ።

6 ይህን ድምፅ ሲሰሙ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም ሰው፣ ሰዎቹ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ፤

7 በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ የሚነጋገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?

8 ታዲያ፣ እያንዳንዳችን በተወለድንበት፣ በራሳችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ቢሆን ነው?

9 እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በመስጴጦምያ፣ በይሁዳ፣ በቀጰዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣

10 በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብጽ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን

11 አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን!”

12 ሁሉም በአድናቆትና ግራ በመጋባት፣ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ።

13 አንዳንዶቹ ደግሞ “ያልፈላ ብዙ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል” በማለት አፌዙባቸው።


ጴጥሮስ ለሕዝቡ ንግግር አደረገ

14 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋራ ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንተ የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ።

15 ጊዜው ገና ከጧቱ ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም!

16 ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤

17 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጨረሻው ቀን፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ።

18 በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሮቼም ላይ፣ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።

19 በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣ አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤ ደምና እሳት፣ የጢስም ዐምድ ይሆናል።

20 ታላቁና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።

21 የጌታን ስም፣ የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’

22 “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ይህን ቃል ስሙ፤ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ታምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል።

23 እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ፤ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።

24 እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና።

25 ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፤ “ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እርሱ በቀኜ ነውና፣ ከቶ አልታወክም።

26 ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል።

27 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም።

28 የሕይወትን መንገድ እንዳውቅ አደረግኸኝ፤ በፊትህም በሐሤት ትሞላኛለህ።’

29 “ወንድሞች ሆይ፤ ከቀደምት አባቶች ዳዊት ሞቶ እንደ ተቀበረ፣ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላችን እንደሚገኝ በድፍረት መናገር እችላለሁ።

30 ነቢይ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ከዘሮቹ አንዱን በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል የገባለት መሆኑን ዐወቀ።

31 ይህን አስቀድሞ በማየቱ እርሱ በሲኦል እንዳልቀረና ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናገረ።

32 ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን።

33 ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።

34 ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ እርሱ ራሱ ግን እንዲህ ብሏል፤ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣

35 “ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” አለው።’

36 “እንግዲህ፣ እግዚአብሔር ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን፣ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ!”

37 ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነካ፤ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ታዲያ ምን እናድርግ?” አሏቸው።

38 ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

39 የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ጌታ አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው፣ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነውና።”

40 በሌላ ብዙ ቃል እየመሰከረላቸው፣ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ” በማለት አስጠነቀቃቸው።

41 ቃሉን የተቀበሉትም ተጠመቁ፤ በዚያ ቀን ሦስት ሺሕ ያህል ሰዎች በቍጥራቸው ላይ ተጨመሩ።


የአማኞች የኅብረት ኑሮ

42 እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር።

43 በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቅና ታምራት ይደረግ ስለ ነበር፣ ሰው ሁሉ ፍርሀት ዐደረበት።

44 ያመኑት ሁሉ በአንድነት ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ የጋራ አደረጉ።

45 ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ይሰጡት ነበር።

46 በየዕለቱ በቤተ መቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፤

47 እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፤ ጌታም የሚድኑትን በቍጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች