1 ዮሐንስ 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየሕይወት ቃል 1 ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዐይኖቻችን ያየነውን፣ የተመለከትነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን። 2 ይህም ሕይወት ተገለጠ፤ እኛም አይተናል፤ እንመሰክራለንም። ከአብ ዘንድ የነበረውን፣ ለእኛም የተገለጠውን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን፤ 3 ያየነውንና የሰማነውን እናንተም ከእኛ ጋራ ኅብረት እንዲኖራችሁ እንነግራችኋለን፤ ኅብረታችንም ከአባት፣ ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ነው። 4 ይህን የምንጽፍላችሁ ደስታችን እንዲፈጸም ነው። በብርሃንና ጨለማ፤ ኀጢአትና ይቅርታ 5 ከርሱ የሰማነው ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በርሱ ዘንድ ከቶ የለም፤ የሚል ነው። 6 ከርሱ ጋራ ኅብረት አለን እያልን በጨለማም ብንመላለስ፣ እንዋሻለን፤ እውነቱንም አናደርግም። 7 ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንመላለስ፣ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል። 8 ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነቱም በእኛ ውስጥ የለም። 9 ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃም ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው። 10 ኀጢአት አልሠራንም ብንል፣ እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ የእርሱም ቃል በእኛ ውስጥ የለም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.