Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 51 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 51
ለመዘምራን አለቃ፤ ዳዊት ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ፣ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ።

2 በደሌን ፈጽሞ ዕጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ።

3 እኔ መተላለፌን ዐውቃለሁና፤ ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው።

4 በቃልህ ትጸድቅ፣ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ፣ አንተን፣ በርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤ በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ።

5 ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ።

6 እነሆ፤ እውነትን ከሰው ልብ ትሻለህ፤ ስለዚህ ጥልቅ ጥበብን በውስጤ አስተምረኝ።

7 በሂሶጵ እርጨኝ፤ እኔም እነጻለሁ፤ ዕጠበኝ፤ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።

8 ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፤ ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው።

9 ፊትህን ከኀጢአቴ መልስ፤ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።

10 አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።

11 ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ።

12 የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ።

13 እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።

14 የድነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤ አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል።

15 ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያውጃል።

16 መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም።

17 እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።

18 በበጎ ፈቃድህ ጽዮንን አበልጽጋት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች ሥራ።

19 የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤ ኰርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች