Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ዮሐንስ 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በእግዚአብሔር ልጅ ማመን

1 ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዷል፤ አባትንም የሚወድድ ሁሉ ልጁንም እንደዚሁ ይወድዳል።

2 እግዚአብሔርን ስንወድድና ትእዛዞቹን ስንፈጽም የእግዚአብሔርን ልጆች እንደምንወድድ በዚህ እናውቃለን፤

3 እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዞቹን መፈጸም ነውና። ትእዛዞቹም ከባድ አይደሉም፤

4 ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው።

5 ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው?

6 በውሃና በደም የመጣው ይህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ በውሃና በደም እንጂ በውሃ ብቻ አልመጣም። የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፤ መንፈስ እውነት ነውና።

7 ስለዚህ ሦስት ምስክሮች አሉት፤

8 እነርሱም መንፈሱ፣ ውሃውና ደሙ ናቸው፤ ሦስቱም ይስማማሉ።

9 የሰውን ምስክርነት ከተቀበልን፣ የእግዚአብሔር ምስክርነት ከዚያም ይልቃል፤ ይህ ስለ ልጁ የሰጠው የእግዚአብሔር ምስክርነት ነውና።

10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ሁሉ በልቡ ምስክር አለው፤ ማንም እግዚአብሔርን የማያምን ሁሉ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውን ምስክርነት ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።

11 ምስክርነቱም ይህ ነው፤ እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሰጠን፤ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው።

12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።


ማጠቃለያ ሐሳብ

13 በእግዚአብሔር ልጅ ስም የምታምኑ እናንተ፣ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤

14 በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ ይሰማናል።

15 የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን፣ የለመንነውንም ነገር እንደ ተቀበልን እናውቃለን።

16 ማንም ሰው ወንድሙ ለሞት የማያበቃ ኀጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይጸልይ፤ እግዚአብሔርም ለሞት የማያበቃ ኀጢአት ላደረጉት ሕይወትን ይሰጣል። ለሞት የሚያበቃም ኀጢአት አለ፤ ስለዚህኛው ግን ይጸልይ አልልም።

17 ዐመፅ ሁሉ ኀጢአት ነው፤ ለሞት የማያበቃም ኀጢአት አለ።

18 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአት እንደማያደርግ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚጠብቀው፣ ክፉውም እንደማይነካው እናውቃለን።

19 እኛ ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን፣ መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደ ሆነ እናውቃለን።

20 የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።

21 ልጆች ሆይ፤ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች