ከመወለድህ በፊት እግዚአብሔር ስለአንተ ያስብ ነበር። እናትህ ሆድ ሳለህ አካላትህን እሱ ፈጥሮ በፍቅር ተመለከተህ። ከጅምሩ ሃሳቡ መልካም ነበር፤ እያንዳንዱን እቅዱን የምታሳካበትን አቅም በአንተ ውስጥ አይቷል። አልተሳሳተም ስለአንተ፤ እስከዚህ ድረስ እንድትደርስ እንድትወለድ ፈቅዶልሃል ምክንያቱም ዓላማው ታላቅ ነው። ከሞት፣ ከአደጋ፣ ከበላይነት፣ ከበሽታ እና ከሱስ ጠብቆሃል። ወደ አስደናቂው ብርሃኑ ጠርቶሃል። የህይወትህ እያንዳንዱ ደረጃ፣ እያንዳንዱ አጋጣሚ በአንተ ላይ ያኖረውን ዓላማ መገለጫ ነው። ዓላማህን ከመፈጸም የሚያግድህ አንተ ራስህ ብቻ ነህ። ምንም ያህል ከባድ ቢመስልም እያንዳንዱ ሁኔታ ለበጎ ነው የሚሰራው። ያሳለፍከው ሁሉ ለወደፊት ህይወትህ መንገድ እያዘጋጀ ነው። እንባህን አብስ፣ ራስህን አትነቅፍ፣ ወደፊት ተመልከት። ካንተ የሚፈልግ ብዙ ሕዝብ አለ። እስካሁን ያሳለፍከው ሁሉ እግዚአብሔር ክፉ ስለሆነ አይደለም፤ ይልቁንም በፍጥነት እንድትፈወስ የሚያግዝህ ነው። እያንዳንዱ ቀን ዓይንህን ስትገልጥ በዚህች ምድር ላይ የምትፈጽመው ታላቅ ዓላማ እንዳለህ በማመን ተነስ። ጥሪህ የክርስቶስን ሙላት እስኪደርስ ድረስ መፈጠርና መቀረጽ ያስፈልገዋል። ከመወለድህ ከረጅም ጊዜ በፊት ህይወትህን ለጠበቀልህ አምላክ ጸንተህ አገልግል።
እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ እንድትሄዱና ፍሬ እንድታፈሩ፣ ፍሬያችሁም እንዲኖር ሾምኋችሁ። ስለዚህም አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል።
እኛ ስላደረግነው አንዳች ነገር ሳይሆን፣ ከዕቅዱና ከጸጋው የተነሣ ያዳነን፣ ወደ ቅዱስ ሕይወትም የጠራን እርሱ ነው። ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፤
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው።
ነገር ግን፣ ከእናቴ ማሕፀን ጀምሮ የለየኝና በጸጋው የጠራኝ እግዚአብሔር፣በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ እንድሰብክ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፣ ከማንም ሥጋ ለባሽ ጋራ አልተማከርሁም፤
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ።የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ።”
እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ።አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ አንድ ሐሳብ ይስጣችሁ፤ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።
ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል።
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል። የተወደደችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት፣ የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣ የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
ሥራው እንዴት እንደ ሆነ ይታያል፤ ምክንያቱም ያ ቀን ወደ ብርሃን ያመጣዋል። በእሳት ስለሚገለጥ እሳቱ የእያንዳንዱን ሰው ሥራ ምንነት ይፈትናል።ማንም የገነባው ሥራ ቢጸናለት ሽልማቱን ይቀበላል፤
ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል።
ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
“ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል።የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።
የተቤዠህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ።
እያንዳንዳችን በአንዱ አካላችን ብዙ ብልቶች እንዳሉን፣ እነዚህም ብልቶች አንድ ዐይነት ተግባር እንደሌላቸው ሁሉ፣እንዲሁም እኛ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን። እያንዳንዳችንም የሌላው ብልት ነን።
እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ።አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን መልሶ ሊያገኝ ይችላልን? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ጥቅም አይኖረውም።“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤
አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።
እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤
በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ ይህም በመጀመሪያ ለአይሁድ፣ ቀጥሎም ለአሕዛብ ነው።በወንጌል የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧልና፤ ጽድቁም ከእምነት ወደ እምነት የሆነ ነው፤ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍጥረትህ ሁሉ ያመሰግንሃል፤ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል።ስለ መንግሥትህ ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ኀይልህም ይነጋገራሉ፤በዚህም ለሰው ልጆች ብርቱ ሥራህን፣ የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ።
እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ አምላክን ፍራ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።መልካምም ይሁን ክፉ፣ ስውር የሆነውን ነገር ሁሉ አንድ ሳይቀር፣ ማንኛውንም ሥራ አምላክ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።
ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ በምንም ነገር አትፍረዱ፤ ጌታ እስኪመጣ ጠብቁ። እርሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያመጣዋል፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውንም ሐሳብ ይገልጠዋል። በዚያ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
እናንተም በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤በዚህም፣ የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን።ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላላወቀው ነው።
ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፤ምክንያቱም የሕይወት መንፈስ ሕግ በክርስቶስ ኢየሱስ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቷችኋል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም።ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤ ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤ ከሚያሳድዱኝም አድነኝ።
ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏል።
እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን።እኔም በብርታት በውስጤ በሚሠራው በርሱ ኀይል ሁሉ እየታገልሁ ለዚህ ዐላማ እጥራለሁ።
እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋራ ሰላም አለን።በርሱም በኩል አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን።
“ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ።የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና።
ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው።
“ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣ መንገዴ እንደ መንገዳችሁ አይደለምና” ይላል እግዚአብሔር።“ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።
እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ።
እኛም ሁላችን ባልተሸፈነ ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያንጸባረቅን፣ የርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው መንፈስ ከሆነ ጌታ ነው።
አሁን እኔ ተቀባይነት ለማግኘት የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? ወይስ ሰዎችን ደስ ለማሠኘት እየተጣጣርሁ ነው? ሰዎችን ደስ ለማሠኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁ ነበር።