2 ጴጥሮስ 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ስምዖን ጴጥሮስ፤ በአምላካችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ በኩል እንደ ተቀበልነው ዐይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉት፤ 2 እግዚአብሔርንና ጌታችን ኢየሱስን በማወቅ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። መጠራትንና መመረጥን ማረጋገጥ 3 በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እርሱን በማወቅ ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የመለኮቱ ኀይል ሰጥቶናል። 4 ከክፉ ምኞት የተነሣ በዓለም ካለው ምግባረ ብልሹ ሕይወት አምልጣችሁ፣ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ በእነዚህ ነገሮች አማካይነት እጅግ ታላቅና ክቡር የሆነውን ተስፋ ሰጥቶናል። 5 በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣ 6 በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣ 7 በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ። 8 እነዚህ ባሕርያት ተትረፍርፈው ቢኖሯችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ዳተኞችና ፍሬ ቢሶች ከመሆን ይጠብቋችኋል። 9 እነዚህ ባሕርያት የሌሉት ግን የሩቁን የማያይ ወይም ዕውር ነው፤ ከቀድሞው ኀጢአቱ መንጻቱንም ረስቷል። 10 ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ለማጽናት ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ምክንያቱም እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም። 11 በዚህም ወደ ጌታችንና አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል። የቅዱሳት መጻሕፍት ትንቢት 12 ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። 13 በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ እናንተን መጐትጐት ትክክል ሆኖ ይታየኛል፤ 14 ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገለጠልኝ ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥዬ እንደምሄድ ዐውቃለሁ፤ 15 እነዚህን ነገሮች ከተለየኋችሁም በኋላ ዘወትር ታስቡ ዘንድ እተጋለሁ። 16 ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀይልና ስለ መምጣቱ የነገርናችሁ የርሱን ግርማ በዐይናችን አይተን እንጂ፣ በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት ተከትለን አይደለም፤ 17 ምክንያቱም ከግርማዊው ክብር “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርና ሞገስ ተቀብሏል፤ 18 እኛም ከርሱ ጋራ በቅዱሱ ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ ይህ ድምፅ ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል። 19 እንግዲያስ ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ፣ በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ እናንተም ለዚህ ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ። 20 ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ልታውቁ ይገባችኋል፤ በመጽሐፍ ያለው የትንቢት ቃል ሁሉ ማንም ሰው በገዛ ራሱ መንገድ የሚተረጕመው አይደለም፤ 21 ምክንያቱም ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.