ኢሳይያስ 2:2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በኋላ ዘመን እንዲህ ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ቤት በተራሮች ራስ ላይ ይታያል፤ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛቡም ሁሉ ወደ እርሱ ይመጣሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዘመኑም ፍጻሜ፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጎርፋሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተሠራበት ተራራ ከሌሎች ተራራዎች ሁሉ በልጦ ይታያል፤ ከኰረብቶችም ሁሉ እጅግ ከፍ ይላል፤ የብዙ መንግሥታት ሕዝቦች ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። |
በዚያም ቀን የእሴይ ሥር ይቆማል፤ የተሾመውም የአሕዛብ አለቃ ይሆናል፤ አሕዛብም በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል።
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝቡ ሁሉ ግብዣን ያደርጋል፤ በዚህ ተራራ ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ፤ የወይን ጠጅንም ይጠጣሉ፤ ዘይትንም ይቀባሉ።
በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦርም የጠፉ፥ በግብፅ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፤ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ።
በዐልን እንደሚያከብሩ፥ ሁልጊዜ ደስ ሊላችሁ፥ ወደ ተቀደሰው ቦታየም ልትሄዱ አይገባችሁምን? በእግዚአብሔር ተራራ ደስ እንደሚላቸው በእንቢልታ ወደ እስራኤል ቅዱስ ልትሄዱ ይገባችኋል።
እርሱም፥ “የያዕቆብን ነገዶች እንደገና እንድታስነሣ፥ ከእስራኤልም የተበተኑትን ወደ አባቶች ቃል ኪዳን እንድትመልስ ባርያዬ ትሆን ዘንድ ለአንተ እጅግ ታላቅ ነገር ነውና፥ እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኀኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ” ይላል።
በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምንም እሰጣቸዋለሁ።”
ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና፥ የሚቃጠለው መሥዋዕታቸውና ቍርባናቸውም በመሠዊያዬ ላይ የተመረጠ ይሆናል።
“እናንተ ግን እኔን ተዋችሁኝ፤ ቅዱሱንም ተራራዬን ረሳችሁ፥ ለአጋንንትም ማዕድ አዘጋጃችሁ፤ ዕድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ቀዳችሁ፤
የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን በምስጋና ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁ ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎዎች፥ በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰችው ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።
እንዲህም ይሆናል፦ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በኢየሩሳሌም በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።
ጌታ ሆይ! አንተ ኀይሌና ረዳቴ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ ነህ፤ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው፥ “በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር ለምንም የማይረባቸውን ጣዖትን ሠርተዋል” ይላሉ።
“ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት ይናገር ነበር፤ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል ብሎ ተናገረ።
ያንጊዜም ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፤ አሕዛብም ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም።
ይመጣሉ፤ በጽዮንም ተራራ ደስ ይላቸዋል፤ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ፥ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ሀገርም ይሰበሰባሉ፤ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይራቡም።
በባቢሎንም ላይ እበቀላለሁ፤ የዋጠችውንም ከአፍዋ አስተፋታለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርስዋ አይሰበሰቡም፤ የባቢሎንም ቅጥሮች ይወድቃሉ።
ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፤ ጎግ ሆይ! በፊታቸው በተቀደስሁብህ ጊዜ፥ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አወጣሃለሁ።
በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፤ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፤ በዚያም ላይ እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር በፊቴ ነበረ።
ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን እግዚአብሔርንና ቸርነቱን ያስቡታል።
ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ እንደ ዓረባ ትሆናለች፣ እርስዋም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው በር ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፣ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፣ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል።
አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።”
በኋለኛዪቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል እግዚአብሔር፦ ሥጋን በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈስሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁ ራእይን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ።
ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ።