Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ራእይ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)


ሁለቱ ምስክሮች

1 በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ “ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ።

2 በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው፤ አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።

3 ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።”

4 እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።

5 ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል፤ ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል።

6 እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፤ ውሕሃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው።

7 ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ያሸንፋቸውማል፤ ይገድላቸውማል።

8 በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል፤ እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።

9 ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኵል በድናቸውን ይመለከታሉ፤ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም።

10 እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስላሠቃዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም ይኖራሉ፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ።

11 ከሦስቱ ቀን ተኵልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው።

12 በሰማይም “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ።

13 በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ከከተማይቱም ዐሥረኛው እጅ ወደቀ፤ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፤ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፤ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ።

14 ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል።


ሰባተኛው መለከት

15 ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል፤”

16 የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው

17 ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ “ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ትልቁን ኀይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤

18 አሕዛብም ተቈጡ፤ ቍጣህም መጣ፤ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፤ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።”

19 በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፤ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፤ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos