ዘኍል 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በለዓምም እስራኤልን መባረክ በእግዚአብሔር ፊት መልካም እንደ ሆነ ባየ ጊዜ፥ እንደ ልማዱ ለማሟረት ወደ ፊት አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን መለሰ። 2 በለዓምም ዐይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዳቸው ሲጓዙ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ። 3 በምሳሌም ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፥ “የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ በትክክል የሚያይ ሰው እንዲህ ይላል፤ 4 “የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ ተኝቶ ዐይኖቹ የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦ 5 ያዕቆብ ሆይ፥ ቤቶችህ፥ እስራኤል ሆይ ድንኳኖችህ ምንኛ ያምራሉ! 6 እንደሚጋርዱ ዛፎች፥ በወንዝ ዳር እንዳሉ የተክል ቦታዎች፥ እግዚአብሔር እንደ ተከላቸው ድንኳኖች በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ናቸው። 7 ከዘሩ ሰው ይወጣል፤ ብዙ ሕዝብንም ይገዛል፥ መንግሥቱም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ትላለች፥ መንግሥቱም ትሰፋለች። 8 እግዚአብሔር ከግብፅ መርቶ አውጥቶታል፤ አንድ ቀንድ እንዳለው ክብር አለው፤ ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፤ አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፤ በፍላጾቹም ጠላቱን ይወጋዋል። 9 አርፎአል፥ እንደ አንበሳና እንደ አንበሳ ደቦል ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? የሚመርቁህ ሁሉ የተመረቁ ይሁኑ፤ የሚረግሙህም ሁሉ የተረገሙ ይሁኑ።” 10 ባላቅም በበለዓም ላይ ተቈጣ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን አለው፦ ጠላቶችን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ 11 እነሆም፥ ፈጽመህ መረቅሃቸው፤ ይህ ሦስተኛህ ነው፤ አሁንም እንግዲህ ወደ ስፍራህ ሂድ፤ እኔ አከብርሃለሁ ብዬ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን እነሆ፥ ክብርህን ከለከለ።” 12 በለዓምም ባላቅን አለው፦ 13 ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞችህ አልተናገርኋቸውምን? 14 አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።” የበለዓም የመጨረሻው ትንቢት 15 በምሳሌም ይናገር ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ በትክክል የሚያይ ሰው እንዲህ ይላል፤ 16 የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም ዕውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ ተኝቶ ዐይኖቹ የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦ 17 አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እባርከዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤ ከእስራኤልም ሰው ይነሣል፥ የሞዓብንም አለቆች ይመታል፤ የሤትንም ልጆች ሁሉ ይማርካል። 18 ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፤ ጠላቱ ኤሳው ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤ እስራኤልም በኀይል ያደርጋል። 19 ከያዕቆብም ኀያል ሰው ይወጣል፤ ከከተማውም የቀሩትን ያጠፋል።” 20 ዐማሌቅንም አይቶ በምሳሌ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “ዐማሌቅ የአሕዝብ አለቃ ነበረ፤ ዘራቸውም ይጠፋል።” 21 ቄኔዎናውያንንም አይቶ በምሳሌ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “ማደሪያህ የጸናች ናት፤ ጎጆህም በአንባ ላይ ተሠርቶአል፤ 22 ቢዖር የጥፋት ጎጆ ቢሆንም አሦር ይማርክሃል።” 23 አግንም ባየው ጊዜ በምሳሌ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ አወይ ማን በሕይወት ይኖራል? 24 ከቄጤዎንም እጅ የሚወጣው አሦርንና ዕብራውያንን ያስጨንቃል፤ እነርሱም በአንድነት ይጠፋሉ።” 25 በለዓምም ተነሣ፤ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም ደግሞ ወደ ቤቱ ገባ። |