ኤርምያስ 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤርምያስ ለፍርድ እንደ ቀረበ 1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ መጣ፤ አለም፦ 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ቁም፤ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ ይሰግዱ ዘንድ ለሚመጡት ለይሁዳ ከተሞች ሁሉ ትነግራቸው ዘንድ ያዘዝሁህን ቃል ሁሉ ተናገራቸው፤ አንዲትም ቃል አታጕድል። 3 ምናልባት እያንዳንዳቸው ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ።” 4 እንዲህም በላቸው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በፊታችሁ በሰጠኋት ሕጌ ትሄዱ ዘንድ ባትሰሙኝ፥ 5 የባሪያዎችን የነቢያትን ቃል ትሰሙ ዘንድ በማለዳ ወደ እናንተ ብልካቸው አልሰማችሁም። 6 ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፤ ይችንም ከተማ ለምድር አሕዛብ ሁሉ ርግማን አደርጋታለሁ።” 7 ካህናቱም፥ ነቢያተ ሐሰትም፥ ሕዝቡም ሁሉ ኤርምያስ በእግዚአብሔር ቤት ይህን ቃል ሲናገር ሰሙ። 8 ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ነገር ሁሉ በፈጸመ ጊዜ ካህናትና ነቢያተ ሐሰት፥ ሕዝቡም ሁሉ፥ “ሞትን ትሞታለህ” ብለው ያዙት። 9 በእግዚአብሔር ስም፥ “ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፤ ይችም ከተማ ባድማ ትሆናለች፤ የሚኖርባትም የለም ብለህ ስለ ምን ትንቢት ተናገርህ?” ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በኤርምያስ ላይ ተሰብስበው ነበር። 10 የይሁዳም አለቆች ይህን በሰሙ ጊዜ ከንጉሡ ቤት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በአዲሱም በእግዚአብሔር ቤት ደጅ መግቢያ ተቀመጡ። 11 ካህናቱና ነቢያተ ሐሰትም ለአለቆቹና ለሕዝቡ ሁሉ፥ “በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁ በዚች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግሮአልና ይህ ሰው ሞት የሚገባው ነው” ብለው ተናገሩ። 12 ኤርምያስም ለአለቆችና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “በሰማችሁት ቃል ሁሉ፥ በዚች ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እናገር ዘንድ እግዚአብሔር ልኮኛል። 13 አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፤ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። 14 እኔ ግን፥ እነሆ በእጃችሁ ነኝ፤ በዐይናችሁ መልካምና ቅን የመሰለውን አድርጉብኝ። 15 ነገር ግን ይህን ቃል ሁሉ በጆሮአችሁ እናገር ዘንድ በእውነቱ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛልና ብትገድሉኝ ንጹሕ ደምን በራሳችሁና በዚች ከተማ፥ በሚኖሩባትም ላይ እንድታመጡ በርግጥ ዕወቁ።” 16 አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያተ ሐሰት፥ “ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮናልና ሞት አይገባውም” አሉ። 17 ከሀገሩ ሽማግሌዎችም ሰዎች ተነሥተው ለሕዝቡ ጉባኤ ሁሉ እንዲህ አሏቸው። 18 “ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት ይናገር ነበር፤ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል ብሎ ተናገረ። 19 በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ እግዚአብሔርን አልፈሩምን? ወደ እግዚአብሔርስ አልተማለሉምን? እግዚአብሔርስ የተናገረባቸውን ክፉ ነገር አይተዉምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።” 20 ደግሞም በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገረ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም የቂርያትይዓሪም ሰው የሸማያ ልጅ ኡርያ ይባል ነበር፤ በዚችም ከተማ፥ በዚችም ምድር ላይ እንደ ኤርምያስ ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገረ። 21 ንጉሡም ኢዮአቄም፥ ሠራዊቱ ሁሉ፥ አለቆቹም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፤ ኡርያም ይህን በሰማ ጊዜ ፈርቶ ሸሸ፤ ወደ ግብፅም ገባ። 22 ንጉሡም ኢዮአቄም ሰዎችን ወደ ግብፅ ላከ፤ የአክቦርን ልጅ ኤልናታንን፥ ሌሎችንም ሰዎች ከርሱ ጋራ ወደ ግብፅ ላካቸው። 23 ከግብፅም ኡርያን አውጥተው ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፤ እርሱም በሰይፍ ገደለው፤ ሬሳውንም በሕዝብ መቃብር ጣለው። 24 ነገር ግን በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች። |