ኤርምያስ 49 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በአሞን ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ 1 ስለ አሞን ልጆች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሚልኮም ጋድን ይወርስ ዘንድ ሕዝቡም በከተሞቹ ላይ ይቀመጥ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች የሉትምን? ወይስ ወራሽ የለውምን? 2 ስለዚህ እነሆ በአሞን ልጆች ከተማ በራባት ላይ የሰልፍ ውካታን የማሰማበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለጥፋትም ትሆናለች፥ መንደሮችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፤ እስራኤልም የወረሱትን ይወርሳል፥ ይላል እግዚአብሔር። 3 ሐሴቦን ሆይ! ጋይ ፈርሳለችና አልቅሽላት፤ እናንተም የራባት ሴቶች ልጆች ሆይ! ሚልኮም፥ ካህናቱና አለቆቹም በአንድነት ይማረካሉና ጩኹ፤ ማቅም ታጠቁ፤ አልቅሱም። 4 ማን ይመጣብኛል ብለሽ በሀብትሽ የታመንሽ አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! በጠፉ ሸለቆዎችሽ ስለ ምን ትመኪያለሽ? 5 እነሆ በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ ፍርሀትን አመጣብሻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እያንዳንዳችሁም በፊታችሁ ወዳለው ስፍራ ትሰደዳላችሁ፤ የሚሸሹትንም የሚሰበስብ የለም። 6 ነገር ግን ከዚያ በኋላ የአሞንን ልጆች ምርኮ እመልሳለሁ ይላል እግዚአብሔር።” 7 ስለ ኤዶምያስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በውኑ በቴማን ጥበብ የለምን? ከብልሃተኞችስ ምክር ጠፍቶአልን? ጥበባቸውስ አልቆአልን? 8 እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ! የዔሳውን ጥፋት፥ የምጐበኝበትን ጊዜ አመጣበታለሁና ሽሹ፤ ወደ ኋላም ተመለሱ፤ በጥልቅም ጕድጓድ ውስጥ ተቀመጡ። 9 ወይን ለቃሚዎች ቢመጡብህ፥ ቃርሚያውን አይተዉልህምን? ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፥ የሚያጠፉት እስኪበቃቸው ድረስ አይደለምን? 10 እኔ ግን ዔሳውን አራቆትሁት፤ የተሸሸጉትንም ስፍራዎች ገለጥሁ፤ ይሸሸግም ዘንድ አይችልም፤ ዘሩም፤ ወንድሞቹም፤ ጎረቤቶቹም ጠፍተዋል፥ እርሱም የለም። 11 ድሃአደጎችህን ተው፤ እኔም በሕይወት አኖራቸዋለሁ፤ መበለቶችህም በእኔ ይታመናሉ። 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ ጽዋውን ያልተገባቸው ሰዎች ጠጥተውታል፤ አንተም መንጻትን ትነጻለህን? እንግዲህ አትነጻም መጠጣትን ትጠጣለህና። 13 ባሶራ ምድረ በዳ፥ መሰደቢያና መረገሚያም እንድትሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከተሞችዋም ሁሉ ለዘለዓለም ባድማ ይሆናሉ። 14 “ከእግዚአብሔር ዘንድ መስማትን ሰምቻለሁ፤ በአሕዛብ ሀገሮች ተሰብሰቡ፤ በእርስዋም ላይ ኑ፤ እርስዋንም ውጓት፥ የሚል መልእክተኛ ተልኳል። 15 እነሆ በሕዝብ ዘንድ የተጠቃህ፥ በሰዎችም ዘንድ የተናቅህ አድርጌሃለሁ። 16 በዓለት ንቃቃት ውስጥ የምትቀመጥ፥ የተራራውን ከፍታ የምትይዝ ሆይ! ድፍረትህና የልብህ ኵራት አነሣሥተውሃል። ቤትህንም ምንም እንደ ንስር ከፍ ብታደርግ፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። 17 “ኤዶምያስም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ የሚያልፍባትም ሁሉ ይደነቃል፤ ስለ መጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጭባታል። 18 ሰዶምና ገሞራ፥ በእነርሱም አጠገብ የነበሩት ከተሞች እንደ ተገለበጡ፥ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር፤ እንዲሁ በዚያ ሰው አይቀመጥም፤ የሰው ልጅም አይኖርባትም። 19 እነሆ ከእርስዋ ዘንድ በቶሎ አባርራቸዋለሁና ከዮርዳኖስ ዳር ወደ ኤታም እንደ አንበሳ ይወጣል፤ ጐልማሶችንም በእርስዋ ላይ እሾማለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ ለእኔ ጊዜን የሚወስን ማን ነው? ወይስ ፊቴን የሚቃወም እረኛ ማን ነው?” 20 ስለዚህ እግዚአብሔር በኤዶምያስ ላይ የመከረባትን ምክር፥ በቴማንም በሚኖሩ ስዎች ላይ ያሰባትን ዐሳብ ስሙ፤ ትንንሾች በጎችን ዘርፈው ይወስዷቸዋል፤ የሚኖሩባትንም ማደሪያቸውን ባድማ ያደርጉባቸዋል። 21 ከመውደቃቸው ድምፅ የተነሣ ምድር ደነገጠች፤ ድምፅዋም እንደ ባሕር ድምፅ እነሆ ተሰማ። 22 እነሆ እንደ ንስር ወጥቶ ይመለከታል፤ ክንፉንም በባሶራ ላይ ይዘረጋል፤ በዚያም ቀን የኤዶምያስ ኀያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል። 23 “ስለ ደማስቆ፤ ክፉ ወሬ ሰምተዋልና ሐማትና አርፋድ አፈሩ፤ ቀለጡም፤ እንደ ባሕርም ተነዋወጡ፤ ያርፉም ዘንድ አይችሉም። 24 ደማስቆ ደከመች፤ ተሸብራም ሸሸች፤ እንቅጥቅጥም ያዛት፤ እንደ ወላድም ሴት ጣርና ምጥ ያዛት። 25 የወደዱትን ቦታና ከተማ እንዴት አልተዉላትም? 26 ስለዚህ ጐበዛዝቷ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፤ በዚያም ቀን ሰልፈኞች ሁሉ ይወድቃሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 27 በደማስቆም ቅጥር ላይ እሳት አነድዳለሁ፤ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች።” 28 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታቸው ስለ ቄዳርና ስለ አሦር መንግሥታት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ተነሡ ወደ ቄዳርም ውጡ፤ የምሥራቅንም ልጆች አጥፉ። 29 ድንኳናቸውንና በጎቻቸውን ይወስዳሉ፤ መጋረጃዎቻቸውንና ዕቃቸውን ሁሉ፥ ግመሎቻቸውንም ለራሳቸው ይወስዳሉ፤ በዙሪያቸውም ሁሉ ጥፋትን ጥሩባቸው። 30 እናንተ በአሦር የምትኖሩ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ተማክሮባችኋልና፥ ክፉ አሳብንም አስቦባችኋልና ሽሹ፤ ወደ ሩቅም ሂዱ፤ በጥልቅ ጕድጓድም ውስጥ ተቀመጡ፥” ይላል እግዚአብሔር። 31 “ተነሡ፤ ዕረፍት ወዳለበት፥ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው፥ ደጅና መዝጊያ፥ መወርወሪያም ወደሌለው፥ ብቻውንም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ዝመቱ። 32 ግመሎቻቸው ለምርኮ ይሆናሉ፤ የእንስሶቻቸውም ብዛት ለጥፋት ይሆናል፤ ጠጕራቸውንም በዙሪያ የሚላጩትን ሰዎች ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከዳርቻቸው ሁሉ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር፥ 33 አሦርም የወፎች መኖሪያና የዘለዓለም ባድማ ትሆናለች፤ በዚያም ሰው አይኖርም፤ የሰው ልጅም አይቀመጥባትም። በኤላም ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ 34 በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በመጀመሪያው ዓመተ መንግሥት ስለ ኤላም ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 35 “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ዋና የኀይላቸው መሣሪያ የሆነውን የኤላምን ቀስት እሰብራለሁ። 36 ከአራቱም ከሰማይ ማዕዘናት አራቱን ነፋሳት በኤላም ላይ አመጣለሁ፤ ወደ እነዚያም ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከኤላም የተሰደዱ ሰዎች የማይደርሱበት ሕዝብ አይገኝም። 37 በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውን በሚሹአት ፊት ኤላምን አስደነግጣለሁ። ክፉ ነገርን እርሱም ጽኑ ቍጣዬን አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እስካጠፋቸውም ድረስ በኋላቸው ሰይፍን እሰድድባቸዋለሁ። 38 ዙፋኔንም በኤላም አኖራለሁ፤ ከዚያም ንጉሡንና መሳፍንቱን አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 39 ነገር ግን በኋለኛው ዘመን እንዲህ ይሆናል፤ የኤላምን ምርኮ እመልሳለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። |