ኢሳይያስ 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የምስጋና መዝሙር 1 እግዚአብሔር አምላኬ፥ ድንቅ ነገርን የዱሮ እውነተኛ ምክርን አድርገሃልና አከብርሃለሁ፤ ስምህንም አመሰግናለሁ። 2 ከተሞችን ትቢያ አደረግህ፤ የተመሸጉ ከተሞችን፥ የኃጥኣንንም መሠረት አፈረስህ፤ ከተሞቻቸውም ለዘለዓለም አይሠሩም። 3 ስለዚህ ድሆች ወገኖች ያከብሩሃል፤ የተገፉ ሰዎች ከተሞችም ያከብሩሃል። 4 ለተዋረዱ ሰዎች ከተሞች ረዳት ሆነሃልና፥ በችግራቸው የተጨነቁትን በደስታ ጋረድሃቸው፤ ከክፉዎች ሰዎችም አዳንሃቸው፤ ለተጠሙት ጥላ ሆንሃቸው፤ ለተገፉትም ሕይወት ሆንሃቸው። 5 ለእነርሱ አሳልፈህ ከሰጠኸን ከኃጥኣን ሰዎች የተነሣ በጽዮን እንደ ተጠሙ አእምሮአቸውን እንዳጡ ሰዎች ሆነናል። 6 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝቡ ሁሉ ግብዣን ያደርጋል፤ በዚህ ተራራ ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ፤ የወይን ጠጅንም ይጠጣሉ፤ ዘይትንም ይቀባሉ። 7 በዚህም ተራራ ላይ ይህን ሁሉ ለአሕዛብ ሰጠ፤ ምክሩ ለአሕዛብ ሁሉ ናትና። 8 ሞት ሰዎችን ዋጠ፤ በረታም፤ እንደ ገናም ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር በአፉ ተናግሮአልና። 9 በዚያም ቀን፥ “እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፤ ያድናልም፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በመዳናችንም ደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን” ይላሉ። 10 እግዚአብሔር በዚህ ተራራ ላይ ዕረፍትን ይሰጠናል፤ እህልም በመንኰራኵር ጭድም በጭቃ እንደሚበራይ እንዲሁ ሞዓብ ይረገጣል። 11 እርሱ ክፉ እንደ አደረገና እንደ አጠፋ በእርሱ ላይ እጁን ያነሣል፤ በእርሱም ላይ እጁን ያነሣው ስድብን ይሽራል። 12 የተመሸገውንና ከፍ ከፍ ያለውንም ቅጥርህን ዝቅ ያደርገዋል። ያዋርደውማል፤ ወደ መሬትም እስከ አፈር ድረስ ይጥለዋል። |