ኤርምያስ 48 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ሞአብ መጥፋት የተነገረ ትንቢት 1 ስለ ሞአብ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ናባው ጠፍታለችና ወዮላት! ቂርያታይም አፍራለች፤ ተይዛማለች፤ መጠጊያዋም አፍራለች፤ ደንግጣማለች። 2 ከእንግዲህ ወዲህ የሞአብ ፈውስ የለም፤ በሐሴቦን ላይ፥ “ኑ ሕዝብ እንዳትሆን እናጥፋት” ብለው ክፉ ነገርን አስበውባታል። ፈጽሞ ትተዋለች፤ ከኋላዋ ሰይፍ ይመጣልና። 3 መፍረስና ታላቅ ጥፋት የሚል የጩኸት ቃል ከሖሮናይም ተሰማ። 4 ሞአብ ጠፍታለች፤ ይህንም በሴጎር ተናገሩ። 5 በሎዊት ዓቀበት ልቅሶ እያለቀሱ ይወጣሉና፥ በሖሮናይምም መንገድ የመባባትን ጩኸት ሰምተዋል። 6 “ሸሽታችሁ ራሳችሁን አድኑ፤ እንደ ሜዳ አህያ በምድረ በዳ ተቀመጡ፤ 7 በሥራሽና በመዝገብሽ ታምነሻልና አንቺ ደግሞ ትያዢያለሽ፤ ካሞሽም ከካህናቱና ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል። 8 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ ጥፋት ወደ ከተማ ሁሉ ይመጣል፤ አንዲትም ከተማ አትድንም፤ ሸለቆውም ይጠፋል፤ ሜዳውም ይበላሻል። 9 በርራ እንድትወጣ ለሞአብ ክንፍ ስጡአት፤ ከተሞችዋም ባድማ ይሆናሉ፤ የሚኖርባቸውም የለም። 10 የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፤ ሰይፉንም ከደም የሚከለክል ርጉም ይሁን። 11 “ሞአብ ከልጅነቷ ጀምራ ዐረፈች፤ በክብርዋም ቅምጥል ነበረች፤ ወይንዋም ከዕቃ ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፤ ወደ ምርኮም አልሄደችም፤ ስለዚህ ቃናው በእርስዋ ውስጥ ቀርቶአል፤ መዓዛዋም አልተለወጠም። 12 ስለዚህ እነሆ ጠማሞችን የምልክበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ይጠሙበታል፤ ጋኖቹንም ይቀጠቅጣሉ፤ ፊቀኖቹንም ይሰብራሉ። 13 የእስራኤልም ቤት ይታመንባት ከነበረው ከቤቴል እንዳፈረ፥ እንዲሁ ሞአብ ከካሞሽ ታፍራለች። 14 እናንተ፦ እኛ ኀያላን በሰልፍም ጽኑዓን ነን እንዴት ትላላችሁ? 15 ሞዓብ ፈርሳለች፤ ከተሞቹዋም ጠፍተዋል፤ የተመረጡትም ጐልማሶችዋ ወደ መታረድ ወርደዋል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 16 የሞአብ ጥፋት ሊመጣ ቀርቦአል፤ መከራውም እጅግ ይፈጥናል። 17 በዙሪያው ያላችሁ ሁሉ ስሙንም የምታውቁ ሁሉ፦ ታላቁ በትር፥ ጠንካራውም ሽመል፥ እንዴት ተሰበረ! ብላችሁ አልቅሱለት። 18 በዲቦን የምትኖሪ ሆይ! ሞአብን የሚያጠፋ ወጥቶብሻልና፥ አምባሽንም ሰብሮአልና ከክብርሽ ውረጂ፤ በጭቃም ላይ ተቀመጪ። 19 በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ! በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፤ የሸሸውንና ያመለጠውን፦ ምን ሆኖአል? ብለሽ ጠይቂው። 20 “ሞአብ ፈርሳለችና አፈረች፤ አልቅሱ፥ ጩኹም፤ ሞአብ እንደ ጠፋች በአርኖን አውሩ። 21 ፍርድ ይመጣል፤ በሜሶር ምድር፥ በኬሎን፥ በያሳና፥ በሜፍዓት ላይ፤ 22 በዲቦን፥ በናባው፥ በቤትዲብላታይም ላይ፥ 23 በቂርያታይም፥ በቤትጋሙል፥ በቤትምዖን ላይ፥ 24 በቂርዮት፥ በቦሶራ፥ በሞአብም ምድር ከተሞች ሁሉ ቅርብና ሩቅ በሆኑ ላይ ፍርድ መጥቶአል። 25 የሞአብ ቀንድ ተሰበረ፤ እጁም ተቀጠቀጠ ይላል እግዚአብሔር። ሞአብ እንደ ተዋረደ 26 “በእግዚአብሔር ላይ ኰርቶአልና፥ አስክሩት፤ ሞአብም በትፋቱ ላይ ይንከባለላል፤ በእጁም ያጨበጭባል፤ ደግሞ መሳቂያ ይሆናል። 27 እስራኤል ለአንተ መሳቂያ አልሆነምን? ወይስ በሌቦች መካከል ተገኝቶአልን? ስለ እርሱ በተናገርህ ጊዜ ራስህን ትነቀንቃለህ። 28 በሞአብ የሚኖሩ ከተሞችን ትተው በዓለት ውስጥ ተቀመጡ፤ በገደል አፋፍም ቤቷን እንደምትሠራ እንደ ርግብ ሆኑ። 29 የሞአብን ስድብ፥ የተዋረደውንም ብዙ ውርደቱን፥ ልቡናውንም ያስታበየበትን ትዕቢቱን ሰምተናል። 30 እኔ ሥራውን አውቃለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ እንደ ኀይሉም መጠን እንዲሁ ያደረገ አይደለም። 31 ሰለዚህ ለሞአብ አለቅሳለሁ፤ ለሞአብም ሁሉ እጮኻለሁ፤ ለቂርሔሬስ ሰዎች አለቅሳለሁ። 32 አንቺ የሴባማ ወይን ሆይ! የኢያዜርን ልቅሶ ለአንቺ አለቅሳለሁ፤ ቅርንጫፎችሽ ባሕርን ተሻግረዋል፤ ወደ ኢያዜርም ባሕር ደርሰዋል፤ ሳይበስል በሰብልሽና በወይንሽ ላይ ጥፋት መጥቶአል። 33 ሐሤትና ደስታ ከፍሬያማው እርሻና ከሞአብ ምድር ጠፍተዋል፤ ወይን ከመጥመቂያው ጠፍቶአል፤ በነግህ የሚጠምቁት የለም፤ በሠርክም የሚያደርጉት የእልልታ ድምፅ የለም። 34 ከሐሴቦን ጩኸት እስከ ኤሊያሊና እስከ ኢያሳ ድረስ ድምፃቸውን ሰጥተዋል፤ ከሴጎር እስከ ሖሮናይምና እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ ይደርሳል፤ የኔምሬም ውኃ ደርቋልና። 35 ሞአብንና በኮረብታው መስገጃ ላይ የሚሠዋውን፥ ለአማልክቱም የሚያጥነውን አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 36 “ያተረፈው ትርፉ ጠፍቶበታልና ስለዚህ ልቤ ለሞአብ እንደ እንቢልታ ይጮኻል፤ ልቤም ለቂርሔሬስ ሰዎች እንደ እንቢልታ ይጮኻል፤ 37 በሰው ሁሉ ራስ ላይ ቡሃነት አለ፤ ጽሕማቸውን ሁሉ ይላጫሉ፤ እጆች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፤ ሁሉም በወገባቸው ማቅን ይታጠቃሉ። 38 ሞአብንም ለምንም እንደማይጠቅም ዕቃ ሰብሬአለሁና በሞአብ ሰገነት ሁሉ ላይ፥ በአደባባዩም ላይ ልቅሶ አለ፥” ይላል እግዚአብሔር። 39 እንዴት ተለወጠች! ከእፍረትም የተነሣ ሞአብ ጀርባዋን እንዴት መለሰች! ሞአብም በዙሪያዋ ላሉት ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ ትሆናለች። 40 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “እነሆ እንደ ንስር ይበርራል፤ ክንፉንም በሞአብ ላይ ይዘረጋል። 41 ሐቄርዮት ተያዘች፤ አንባዎችዋም ተወስደዋል፤ በዚያም ቀን የሞአብ ኀያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል። 42 ሞአብም በእግዚአብሔር ላይ ኰርታለችና ሕዝብ ከመሆን ትጠፋለች። 43 በሞአብ የምትኖር ሆይ! ፍርሀትና ጕድጓድ፥ ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 44 እርስዋን በምጐበኝበት ዓመት በሞአብ ላይ ይህን አመጣለሁ፤ በፍርሀት የሸሸ በጕድጓድ ውስጥ ይወድቃል፤ ከጕድጓድም የወጣ በወጥመድ ይያዛል፤ ይላል እግዚአብሔር። 45 ከሰልፍ የሸሹ ከሐሴቦን ጥላ በታች ቆመዋል፤ እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ወጥቶአል፤ የሞአብንም ማዕዘን፥ የሚጮኹ ልጆችንም ራስ በልቶአል። 46 ሞአብ ሆይ! ወዮልሽ! የካሞሸ ወገን ጠፍቶአል፤ ወንዶች ልጆችሽ ተማርከው ተወስደዋልና፥ ሴቶች ልጆችሽም ወደ ምርኮ ሄደዋልና። 47 ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የሞአብን ምርኮ እመልሳለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። የሞዓብ ፍርድ እስከዚህ ድረስ ነው። |