መዝሙር 48 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 አሕዛብ ሁላችሁ፥ ይህን ስሙ፤ በዓለም የምትኖሩም ሁላችሁ፥ አድምጡ፤ 2 የሰው ልጆች ባለጠጎችና ድሆች፥ በየሀገራችሁ በአንድነት። 3 አፌ ጥበብን ይናገራል፥ የልቤም ዐሳብ ምክርን፥ 4 በጆሮዬ ምሳሌ አደምጣለሁ፥ በበገናም ነገሬን እገልጣለሁ። 5 ከክፉ ቀን ለምን እፈራለሁ? ኀጢአት ተረከዜን ከበበኝ፤ 6 በኀይላቸው የሚታመኑ፥ በባለጠግነታቸውም ብዛት የሚኮሩ፤ 7 ወንድም ወንድሙን አያድንም፥ ሰውም አያድንም፤ ቤዛውንም ለእግዚአብሔር አይሰጥም፥ 8 የነፍሱንም ዋጋ ለውጥ፥ 9 በዓለም የደከመ ለዘለዓለም ይድናል፥ ጥፋትን አያይምና። 10 ጠቢባንን ሲሞቱ ባየሃቸው ጊዜ፥ እንደዚሁ ልብ የሌላቸው ሰነፎች ይጠፋሉ፥ ገንዘባቸውንም ለሌሎች ይተዋሉ። 11 መቃብራቸው ለዘለዓለም ቤታቸው ነው፥ ማደሪያቸውም ለልጅ ልጅ ነው፤ በየሀገራቸውም ስማቸው ይጠራል። 12 ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ፥ መሰላቸውም። 13 በአፋቸው ሲወዱ፥ ራስዋ መንገዳቸው መሰናክላቸው ናት፥ 14 እንደ በጎች ሞት በሲኦል ይጠብቃቸዋል፥ ቅኖችም በማለዳ ይገዙአቸዋል፥ ረድኤታቸውም ከክብራቸው ተለይታ በሲኦል ትጠፋለች። 15 ነገር ግን በሚወስዱኝ ጊዜ እግዚአብሔር ነፍሴን ከሲኦል እጅ ያድናታል። 16 በበለጸገ ጊዜ፥ የቤቱም ክብር በበዛ ጊዜ ሰውን አትፍራው፥ 17 በሚሞት ጊዜ ከእርሱ ጋር ምንም አይወስድምና፥ የቤቱም ክብር ሁሉ ከእርሱ ጋር አይወርድምና። 18 በሕይወቱ ሳለ ሰውነቱ ደስ ብሎአታልና ሰው መልካም ብታደርግለት ያመሰግንሃል። 19 ወደ አባቶቹም ዓለም ይወርዳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ብርሃንን አያይም። 20 ሰው ግን ክቡር ሲሆን አላወቀም። ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ፥ መሰላቸውም። |