ዕብራውያን 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሥጋዌ ምሥጢር 1 ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ። 2 በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፥ ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን። 3 እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የመልኩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ ኀጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ፥ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። 4 በዚህን ያህል መብለጥ ከመላእክት በላይ ሆኖ ከስማቸው የሚበልጥና የሚከብር ስምን ወረሰ። 5 ከመላእክትስ ከሆነ ጀምሮ፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” ዳግመኛም፥ “እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጄ ይሆነኛል” ያለው ከቶ ለማን ነው? 6 ዳግመኛም በኵርን ወደ ዓለም በላከው ጊዜ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል” አለ። 7 ስለ መላእክቱም፥ “መላእክቱን ነፋሳት፥ የሚላኩትንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው እርሱ ነው” አለ። 8 ስለ ልጁ ግን፥ “ጌታ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የጽድቅ በትር ነው” አለ። 9 “ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክህ እንዳንተ ካሉት ይልቅ የሚበልጥ የደስታ ዘይትን ቀባህ።” 10 ዳግመኛም እንዲህ አለ፥ “አቤቱ አንተ አስቀድሞ ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። 11 እነርሱ ያልፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃል፤ 12 እንደ መጋረጃም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ይለወጣሉም፤ አንተ ግን መቼም መች አንተ ነህ፤ ዘመንህም የማይፈጸም ነው።” 13 ከሆነ ጀምሮ ከመላእክት፥ “ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስከ አደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ማንን አለው? 14 መላእክት ሁሉ መናፍስት አይደሉምን? የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ስለ አላቸው ሰዎችስ ለአገልግሎት ይላኩ የለምን? |