ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ተረፈ ባሮክ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 አቤሜሌክም ኤርምያስ ከላከው ቦታ በቀትር ጊዜ በለሱን አመጣ፤ ጽፍቅ ያለች ዱርንም አገኘ፤ ጥቂትም ያርፍ ዘንድ በጥላዋ ስር ተቀመጠ፤ በለስ ያለባትንም ሙዳይ ተንተርሶ ስድሳ ስድስት ዓመት ተኛ፤ ከመኝታውም አልነቃም። 2 ከዚያም ዘመን በኋላ ከመኝታው ነቅቶ ተነሣ፤ “ገና ራሴን ይከብደኛልና፥ እንቅልፌንም አልጨረስሁምና ዳግመኛ ጥቂት ልተኛ” አለ። 3 ያንም የበለሱን ሙዳይ ከፈተ፤ በለሶችም አዲስ ሆነው፥ ወተታቸውም ሲፈስስ አገኘ፤ ራሱንም ከብዶት ነበርና እንቅልፉንም አልጨረሰምና ይተኛ ዘንድ ወደደ። 4 እንዲህም አለ፥ “ተመልሼ እንዳልተኛ እንዳልዘገይም እፈራለሁ፤ አባቴ ኤርምያስ ተግቶ በጧት ልኮኛልና እንዳይቈጣኝ እፈራለሁ። 5 ሙቀት ሆኗልና፥ በሁሉም የሚተውበት ጊዜ የለምና አሁን ተነሥቼ እሄዳለሁ።” 6 ተነሥቶም የበለሱን ሙዳይ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገባ። ከተማውንም ቤቱንም አላወቀም። 7 ጽኑ ድንጋጤ መጥቶበታልና “አቤቱ፥ አንተ የተመሰገንህ ነህ” አለ። 8 እንዲህም አለ፥ “ይህቺ ከተማ ኢየሩሳሌም አይደለችምን? በተራራው ጎዳና መጥቻለሁና፥ ራሴንም ከብዶኛልና፥ እንቅልፌንም አልጨረስሁምና አእምሮዬን ዘንግቼ ምናልባት ተስቶኝ ይሆን? 9 ከተማዪቱ ባዕድ እንደ ሆነችብኝ በኤርምያስ ዘንድ ይህን ነገር እንዴት እናገራለሁ?” ኢየሩሳሌምም እንደ ሆነች በከተማው ያለውን ምልክት ሁሉ ፈለገ። 10 ዳግመኛም ወደ ከተማ ተመለሰ፤ የሚያውቀውም እንዳለ ፈለገ፤ ነገር ግን አላገኘም፤ “ታላቅ ድንጋጤ በእኔ መጥቶብኛልና አቤቱ፥ አንተ የተመሰገንህ ነህ” አለ። 11 ሁለተኛም ከከተማ ርቆ ወጣ፤ እያዘነም ተቀመጠ፤ ሲሄድም አያውቅም ነበር፤ የበለሱንም ሙዳይ አኖረ፤ “ይህን ድንቁርና እግዚአብሔር ከእኔ እስኪያርቅልኝ ድረስ በዚህ እቀመጣለሁ” አለ። 12 ከዚህ በኋላ ተቀምጦ ሳለ አንድ ሽማግሌ ሰው ከምድረ በዳ ሲመለስ አየ። 13 አቤሜሌክም እንዲህ አለ፥ “አንተ ሽማግሌ፥ ይቺ ከተማ ማን ናት? ብዬ እጠይቅሃለሁ።” 14 ያም ሽማግሌ፥ “ኢየሩሳሌም ናት” አለው፤ “ያገኘሁት ሰው የለምና የእግዚአብሔር ካህን ኤርምያስ ወዴት አለ? ሌዋዊው ባሮክና የከተማው ሕዝብ ሁሉስ ወዴት አሉ?” አለው፤ 15 ሽማግሌውም እንዲህ አለው፥ “አንተ ከዚች ከተማ አይደለህምን? ይህን ያህል ዘመን ኖረህ የእርሱን ነገር ትጠይቅ ዘንድ ኤርምያስን ዛሬ ማን ዐሰበው? 16 ተማርኮ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ ተሰጥቶአልና፤ እስራኤልንም ያስተምር ዘንድ ወደ ባቢሎን ሄዶአልና ኤርምያስስ ከሕዝቡ ጋር በባቢሎን አለ።” 17 አቤሜሌክም ያንጊዜ ከዚያ ከሽማግሌው ይህን ቃል ሰማ። 18 አቤሜሌክም እንዲህ አለው፥ “ሰውን፥ ይልቁንም ሽማግሌውን ሰው ሊንቁት አይገባም እንጂ አንተ ሽማግሌ ሰው ባትሆን በሰደብሁህ ነበር፤ በአንተም በዘበትሁብህ ነበር፤ ያም ባይሆን አእምሮውን ያጣ ሽማግሌ ብዬ በሰደብሁህ ነበር። 19 ሕዝቡ ተማርከው ወደ ባቢሎን ሄዱ፤ ስለምትለውስ ነገር የሰማይ ሻሻቴ እንኳ በእነርሱ ላይ ቢወርድ ወደ ባቢሎን ተማርከው ይሄዱ ዘንድ ጊዜው አይደለም። 20 አንተ ግን ተማርከው ወደ ባቢሎን ሄዱ ትላለህ፤ በሕዝቡ ዘንድ ላሉ ለበሽተኞች እንሰጥ ዘንድ አባቴ ኤርምያስ እኔን እንደ ላከኝ ጥቂት በለስ ላመጣ ወደ አግሪጳስ ወይን ቦታ ሄድሁ። 21 ሄጄም ከዚያ ደረስሁ፤ ያዘዘኝንም ይዤ ተመለስሁ፤ ስሄድም አንዲት ዛፍ አገኘሁ፤ የቀትር ጊዜ ነበርና በበታችዋ ዐርፍ ዘንድ ተቀመጥሁ። 22 ከዚያም የበለሱን ሙዳይ ተንተርሼ ተኛሁ፤ ከእንቅልፌም በነቃሁ ጊዜ የዘገየሁ መሰለኝ፤ የበለሱንም ሙዳይ ከፍቼ አየሁ፤ መርጬ እንደለቀምኋቸው ወተቱ ሲፈስስ አገኘሁት። 23 እነሆ፥ አንተ ሕዝቡ ተማርከው ወደ ባቢሎን ሄዱ ትላለህ፤ እነሆ፥ በለሱ እንዳልጠወለገ እይ” ብሎ የበለሱን ሙዳይ ከፍቶ አሳየው። 24 ሽማግሌውም በለሱ አዲስ እንደ ሆነ፥ ወተቱም እንደሚፈስስ አየ፤ ያንጊዜም ሽማግሌው አደነቀ። 25 አቤሜሌክንም እንዲህ አለው፥ “ልጄ፥ አንተ ደግ ሰው ነህ፤ ፈጣሪህ የዚህችን ከተማ ጥፋት ሊያሳይህ አልወደደምና አምላክ ለአንተ መረጋጋትን አምጥቶ አድኖሃል። 26 እነሆ፥ ሕዝቡ ወደ ባቢሎን ተማርከው ከሄዱ ዛሬ ስድሳ ስድስት ዓመት ሆነ። 27 ልጄ፥ ፈጽመህ ልታውቅስ ከወደድህ ዘሮችዋ እንደ በቀሉ ወደ እርሻዎች ፈጽመህ ተመልከት፤ የበለስም ጊዜው አይደለም፤” ያንጊዜ አቤሜሌክ የዚህ ሁሉ ጊዜው እንዳልሆነ ዐወቀ። 28 ቃሉንም አሰምቶ፥ “የሰማይና የምድር አምላክ፥ በሀገሩ ሁሉ ያሉ የጻድቃን ነፍሳት ዕረፍታቸው የሆንህ ጌታዬና አምላኬ ሆይ፥ አመሰግንሃለሁ፥” አለ። 29 ሽማግሌውንም፥ “ይህ ወር ምንድን ነው?” አለው፤ እርሱም፦ የኔሳን ወር ዐሥራ ሁለተኛው ቀን፥ ይኸውም ሚያዝያ ነው” አለው። 30 ከዚህም በኋላ አቤሜሌክ ለዚህ ሽማግሌ ከበለሶቹ ሰጠው፤ እርሱም፥ “አምላክ ወደ ሰማያዊት ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ይምራህ” አለው። |