የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


መጽሐፈ ሲራክ 39 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
መጽሐፈ ሲራክ 39

ጸሐፍት

1 የልዑል እግዚአብሔርን ሕግ የሚያጠናና የሚመረምር፥ እንዲህ አይደለም፤ የጥንታውያኑን ሰዎች ጥበብ ያጠናል፥ ትንቢቶችንም ይመረምራል።

2 የዝነኛ ሰዎች ንግግሮችን በወጉ ይይዛል፥ ምሳሌችን ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃል።

3 የምሳሌዎቹን ምሥጢራት ይመረምራል፥ እንቆቅልሻቸውንም ይፈታል።

4 ልዑላኑን ያገለግላል፥ መሪዎች ባሉበትም አይጠፋም። ወደ ውጭ ሀገሮችም ይጓዛል፥ የሰውን ደግነትና ክፋት ጠንቅቆ ያውቃል።

5 ንጋት ላይ በንጹሕ ልቡ ወደ ፈጣሪው ወደ እግዚአብሔር ፊቱን ይመልሳል፤ በልዑል እግዚአብሔር ፊት ልመናውን ያቀርባል፥ አፉንም የሚያሟሸው በጸሎት ነው፥ ስለ ኃጢአቱም ይቅርታን ይለምናል።

6 የታላቁ እግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ከሆነ፤ እርሱ በእውቀት መንፈስ ይሞላል፥ የጥበብን ቃላት ያዘንበል፥ በጸሎቱም እግዚአብሔርን ያመሰግናል።

7 በዓላማና በትምህርት ትክክለኛ ሆኖ ያድጋል፤ የእግዚአብሔርን ድብቅ ምሥጢራት ጠልቆ ይመረምራል።

8 የተማረውን በውል ያስመሰክራል፤ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕግም ይኩራራል።

9 ብዙዎች ዕውቀቱን ያመሰግኑለታል፤ ፈጽሞ የሚረሳም አይደለም፤ መታሰቢያውም አይጠፋም፤ ከትውልድ ወደ ትውልድም ስሙ ሕያው ሆኖ ይኖራል።

10 ሀገሮች ጥበቡን ያደንቃሉ፤ በጉባኤ ፊት ይመሰገናል።

11 ዕድሜ ከሰጠው ስሙ ከሌሎች ሺህ ስሞች የበለጠ የተከበረ ይሆናል፥ ቢሞትም ይኸው ይበቃዋል።

እግዚአብሔርን የማመስገን ጥሪ

12 ቀሪዎቹ ሐሳቦቼን እነሆ አቀርባለሁ፥ ሞልታ እንደምትታየው ጨረቃ ሙሉ ሆኛለሁ!

13 ጻድቃን ልጆቼ ሆይ ስሙኝ! በወንዝ ዳር እንደ በቀለ ጽጌሬዳ እናንተም አብቡ።

14 የዕጣንን መልካም ሽታ ይስጣችሁ፥ እንደ ነጭ አበባ አብቡ፥ መዓዛችሁ ዙሪያችሁን ያውድ፥ የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፥ ስለ ሥራዎቹ ሁሉ እግዚአብሔርን ባርኩ።

15 የስሙን ታላቅነት አውጁ፥ በመዝሙርና በክራር እርሱን አመስግኑ፥ ምስጋናውንም የምታዜሙት እንዲህ በማለት ነው፥

16 የእግዚአብሔር ሥራዎች ምንኛ ድንቅ ናቸው? ትዕዛዛቱም ሁሉ በጊዜአቸው ይፈጸማሉ! ይህ ምንድነው? ይህስ ለምን ተፈጸመ? ማለት አይገባህም፤ ለሁሉም ጥያቄ ጊዜ አለው።

17 ቃሉን በሰማ ጊዜ ውሃው ይቆማል፤ ከፍ እያለም ይከማቻል፥ ድምፁን በሰሙ ጊዜ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ይፈጠራሉ።

18 በእርሱ ትእዛዝ የፈቀደው ሁሉ ይፈጸማል፤ ማዳን ከፈለገ የሚገታው የለም።

19 የሰው ልጅ የሚሠራውን ሁሉ ያያል፤ ከዐይኖቹ ሊሠወር የሚችል ከቶ ምንም የለም።

20 እይታው መጨረሻም መጀመሪያም የለውም፤ አንድም ነገር ከቶ አያስደንቀውም።

21 ይህ ምንድነው? ያስ ለምን ሆነ? ማለት አይገባህም፤ ሁሉም ነገር የተፈጠረው በምክንያት ነውና።

22 ምርቃቱ ደረቁን መሬት እንደ ወንዝ እንደሚያርሰው፤ እንደ ጐርፍም እንደሚያጥለቀልቀው ሁሉ፥

23 ቅጣቱም እንዲሁ ውሃን ወደ ጨው እንደቀየረ፥ ለአሕዛብ የሚሰጣቸው ውርሱ ነው።

24 መንገዶቹ ሁሉ ለጻድቃን የተስተካከሉ፥ ለኃጥአን በመሰናክል የተሞሉ ናቸው።

25 መልካሙ ሁሉ ለደጋጐች፥ መጥፎው ሁሉ ለክፉዎች የተፈጠረ ነው።

26 ለሰው ሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች፥ ውሃና እሳት፥ ብረትና ጨው፥ የስንዴ ዱቄት፥ ወተትና ማር፥ የወይን ጭማቂ፥ ዘይትና ልብስ ሲሆኑ፥

27 እነኚህ ሁሉ ለጻድቃን ጥሩ፤ ለኃጢአተኞች ግን መጥፎ ናቸው።

28 ለቅጣት የተፈጠሩ ነፍሳት አሉ፤ በተቆጣም ጊዜ በመቅሰፍትነት ይልካቸዋል፤ በጥፋት ቀን ኃያልነታቸውን ያሳያሉ፤ የፈጣሪያቸውንም ቁጣ ያበርዳሉ።

29 እሳትና ብርድ፥ ረኀብና ሞት፥ የተፈጠሩት ለቅጣት ነው።

30 የአራዊት ጥርሶች፥ ጊንጦችና እፉኝቶች፥ ኃጢአተኞችን የሚያጠፉ የበቀል ሠይፍ ናቸው።

31 ትእዛዛቱን በመፈጸም ሁሉም ይደሰታሉ፤ በምድር ላይ ባስፈላጊው ጊዜ ሁሉ ዝግጁዎች ናቸው፤ ጊዜያቸው በደረሰ ጊዜም ከቃሉ አይወጡም።

32 እኔም ከመነሻዬ የቆረጥኩት ለዚሁ ነው፤ የተመራመርኩት፥ የጻፍኩትም ከዚህ በመነጨ ነው።

33 የእግዚአብሐር ሥራዎች ሁሉ መልካም ናቸው፤ ጊዜው በደረሰ ጊዜ አስፈላጊውን ሁሉ ይሰጣል።

34 “ይኸኛው ከዚያኛው የባስ ነው” ማለት የለብህም፤ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ሁሉም ምንነቱን ያሳያል።

35 እንግዲህ አሁን በሙሉ ልበ፥ ለዛ ባለው ድምፅ፥ የእግዚአብሔርን ስም ባርክ።