Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 38 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሕክምናና በሽታ

1 አገልግሎቱን በማየት የእግዚአብሔርም ፍጡር በመሆኑ፥ ሐኪሙን በሚገባ አክብረው።

2 ከንጉሥ እንደሚቀበሉት ስጦታ ፈውስ የሚገኘውም ከታላቁ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

3 የሐኪሙ እውቀት ያኮራዋል፤ ታላላቅ ሰዎችም ያከብሩታል።

4 እግዚአብሔር ፈውስ የሚሆኑ ሥራ ሥሮችን ከመሬት አፈራ፤ አዋቂ ሰውም አይንቃቸውም።

5 የእንጨት ቁራጭ ኃይሉን ለማሳየት፥ ውሃውን ጣፋጭ አላደረገምን?

6 ከታላላቅ ሥራዎቹ ይጠቀሙ ዘንድ፥ ለአንዳንድ ሕዝቦች እግዚአብሔር ዕውቀትን ሰጥቷል።

7 ሥራ ሥሮች ፈውስ ይሆናሉ፤ ሕመምንም ያስታግሳሉ፤ ሐኪሙም ይቀምማቸዋል።

8 ለእግዚአብሔር ሥራ ፍጻሜ የለውም፤ ለእርሱ ምስጋና ይግባውና ጤንነት በዓለም ሰፍኗል።

9 ልጄ ሆይ! በታመምህ ጊዜ ዐመፀኛ አትሁን፤ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፤ እርሱም ያድንሃል።

10 ከበደል ራቅ፤ እጆችንም አታሳድፍ፤ ልብህንም ከኃጢአት ሁሉ አንጻ።

11 ዕጣንንና የመታሰቢያ ዱቄት ስጥ፤ አቅምህ የፈቀደውን የተሻለ መሥዋዕት አቅርብ።

12 ከዚህ በኋላ ወደ ሐኪም ሂድ፤ እርሱንም የፈጠረው እግዚአብሔር ነውና። ያስፈልግሃልና ካንተ አይራቅ።

13 መልካም ጤንነት በሀኪሞች ብርታት የሚወሰንበት ወቅት አለ።

14 እነርሱም በተራቸው ፈውስን ይሰጡ ዘንድ፥ ያድኑ፥ ዕድሜንም ይቀጥሉ ዘንድ፥ እግዚአብሔር የማዳን ሞገስን ይሰጣቸው ዘንድ፥ ይጸልያሉና።

15 በፈጣሪው ፊት ኃጢአት የሚሠራ፥ በሐኪም እጅ ይውደቅ!


ኀዘን

16 ልጄ ሆይ! ስለ ሞተ ሰው አልቅስ፤ ኀዘንህንም በእንጉርጉሮ አሰማ፤ በተገቢው ሥርዓት አስክሬንን ቅበር፤ መቃብሩንም አክብር።

17 አምርረህ አንባ፤ ደረትህን ድቃ፤ ከሰው ሐሜት እንድትድን፥ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን፥ ለሟች የሚገባውን ኀዘን አድርግ። ከዚህ በኋላ ግን ተጽናና።

18 መሪር ኀዘን ሞትን ያመጣል፤ ሰቆቃ የበዛበት ልብም ትደክማለችና።

19 በመከራ ጊዜ ኀዘን ይጸናል፤ የስቃይ ሕይወት ሸክሙ ይከብዳል።

20 ልብህን በኀዘን አታሰቃይ፤ ገለል አድርገው፤ ፍጻሜህን አስብ።

21 መመለስ እንደሌለ አትዘንጋ፤ ሟቹን ማዳን አትችልም፤ ራስህንም ትጐዳለህ።

22 ዕጣዬን አስታውስ፤ ያንተም ዕጣ ይኸው ነውና፥ እኔ ትናንት አንተ ደግሞ ዛሬ!

23 ሙታን አንዴ ካረፉ፥ መታሰቢያውም እንዲሁ ይሁን፤ መንፈሳቸው ከራቀ በኋላ ስለ እነርሱ አትዘን።


የተለያዩ ሙያዎችና የእጅ ጥበብ

24 ጸሐፊው በትርፍ ጊዜው ጥበብን ይቀስማል፤ በሥራ ይልተጠመደ ሰው ጥበበኛ ሊሆን ይችላል።

25 እርፍ የሚጨብጥ፥ ፎላጐቱ በዘንጉ መጠቀም የሆነ፥ በሥራ የተጠመዱትን በሬዎች የሚነዳ፥

26 ስለ ቀደዳቸው ፈሮች ብዙ የሚያስብ፥ ሌቱን ጊደሮቹን ለማደለብ የሚተጋ፥ ገበሬ እንደምን ጥበበኛ ይሆናል?

27 ሠራተኞችና የእጅ ባለሙያዎችም፥ ቀን ከሌት ይደክማሉና እንዲሁ ናቸው። ማኀተሞች የሚቀርጹ፥ አዳዲስ ንድፋቸውንም መልሰው የሚቀርጹ፥ ሥራቸውንም ለማጠናቀቅ ሌትም የሚሠሩ፤ ባተሌዎች በመሆናቸው ጥበብን ለመቅሰም ጊዜ አይኖራቸውም።

28 ከመስፉ አጠገብ የሚቀመጠውም አንጥረኛ እንዲሁ ነው። ከብረቱ ምን እንደሚቀርጽ ያስባል፥ የእሳቱ ወላፈን ቆዳውን ይለበልበዋል፥ ከወናፉ ሙቀትም ጋር ይታገላል፥ የመዶሻው ድምፅ ያደነቁረዋል፥ ዐይኖቹም በሚያወጣቸው ቅርጾች ላይ ተተክለዋል፥ ቀልቡን በሥራው ላይ ያሳርፋል፥ ሥራውንም በሚገባ ካላጠናቀቀ ቢመሽ እንኳ አያርፍም።

29 ሥራውን በትጋት የሚሠራውም ሸክላ ሰሪ እንዲሁ ነው፤ መንኮራኮሩን በእግሩ ያሸከረክራል፥ ያለማቋረጥ ሥራውን ይከታተላል፥ እያንዳንዷ የጣት እንቅስቃሴ የተጠናች ነች።

30 ጭቃውን በክንዱ ይጠፈጥፈዋል፥ በእግሩ ያባካዋል፥ በሚገባም ይለቀልቀዋል፥ ማድረቂያውንም ሲያጸዳ ያመሻል።

31 እኒህ ሰዎች ሁሉ በእጆቻቸው ይተማመናሉ፤ እያንዳንዱም በየሙያው አዋቂ ነው።

32 አንዲት ከተማ ያለእነርሱ ሰው ሊኖርባት አይችልም፤ በዚያም ሰፈር ማድረግ፥ መጓዝም አይቻልም።

33 በምክር ቤቱ ውስጥ ግን እነርሱን አታገኛቸውም፤ በጉባኤውም ውስጥ ሥልጣን የላቸውም፤ በዳኝነት ወንበር ላይ አይቀመጡም፤ የሕጉን አሠራርም አያውቁም፤

34 ባህላቸው ወይም ፍርዳቸው የሚመረጥ አይደለም፤ ከፈላስፎችም ዘንድ አዘውትረው አይቀርቡም፤ የምድርን ወጋግራዎች ይደግፋሉ፤ ጸሎታቸውም ስለ ሥራቸው ነው።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች