ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 40 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሰው ምስኪንነት 1 የመከራ ዕጣ ለሰዎች ተፈጥሯል፤ በአዳም ልጆች ላይ ከባድ ቀንበር ተጭኗል፤ ከእናታቸው ማሕፀን ከወጡበት ዕለት ጀምሮ፥ ወደ ሁሉም እናት እስኪመለሱ ድረሰ፥ እንዲሁ ይኖራሉ። 2 እነርሱን የሚያስጨንቅ፥ ልባቸውንም የሚያሸብር፥ ዕለተ ሞታቸው ነው። 3 በከበረ ዙፋን ላይ ከተቀመጠው ሰው ጀምሮ፥ በትቢያና በአመድ ላይ እስከወደቀው ምስኪን ድረስ፥ 4 ከፋይ ከለበሰው፥ ዘውድ ከደፋው ጀምሮ፥ ማቅ እስከለበሰው ድረስ ቁጣና ቅናት፥ ብጥብጥና ሁከት፥ የሞት ፍርሃት፥ ምቀኝነት፥ ግጭትም በሰፊው ነግሠዋል። 5 ሌት እንኳ ባልጋው ላይ ባረፈ ጊዜ፥ መኝታው ጭንቀቱን ያባብስበታል። 6 ለማረፍ እንደተጋደመ ብዙም ሳይቆይ፥ እንደ ቀኑ ሁሉ በእንቅልፍ ልቡም ቅዠቶች ያስጨንቁታል፤ ከጦርነት እንዳመለጠ፥ 7 በማምለጥም ላይ ሳለ እንደነቃና የሚያስፈራም ነገር ባለ መኖሩ የተደነቀ ሰውን ይመስላል። 8 ለሰውና ለእንስሳት፥ ለሁሉም ፍጥረታት፥ ሰባት ጊዜ እጥፍ ደግሞ ለኃጢአአተኞች፥ 9 ሞትና ደም፥ ፀብና ሰይፍ፥ ጥፋትና ረሃብ፥ መከራና መዓት ይጠብቋችኋል። 10 እነኚህ ሁሉ የተፈጠሩት ለኃጥአን ነው፤ የጥፋት ውሃ የወረደውም በእነርሱ ምክንያት ነው። 11 ከምድር የተገኘ ሁሉ ወደ ምድር፥ ከውሃም የተገኘ ወደ ባሕር ይመለሳል። ልዩ ልዩ ምሳሌዎች 12 ጉቦና ፍትሕ ማጓደል ሁሉ ይወገዳሉ፤ መልካም እምነት ግን ለዘለዓለም ይኖራል። 13 ያለ አግባብ የተገኘ ሃብት እንደ ወራጅ ውሃ፥ የዝናቡን መምጣት እንደሚያበስርም ነጐድጓድ ብልጭ ብሎ ይጠፋል። 14 እጁን ሲዘረጋ ይደሰታል፤ ኃጢአተኞችም ያኔውኑ በቅጽበት ይጠፋሉ። 15 የክፉ ሰዎች ቀንበጦች፥ ቅርንጫፎቻቸው አይበዙም፤ የተበከሉ ሥሮች የሚያጋጥማቸው ጠንካራ ዓለት ብቻ ነው። 16 በወንዝ ጠርዝ ላይና በሐይቅ ዳር የሚበቅል ሸምበቆ፥ ከሚነቅሉት ተክሎች የመጀመሪያው ነው። 17 ቸርነት ዋነኛው የምርቃት ገነት ነው፤ ምጽዋትም ዘለለማዊ ነው። 18 የግል መተዳደሪያ ላለውና ጠንክሮ ለሚሠራ ሰው፥ ሕይወት አስደሳች ነች። ሀብት ያገኘ ደግሞ ከሁለቱም የተሻለ ነው። 19 ልጆች መውለድና ከተማን መቆርቆር ስምን ያስጠራል፤ ንጹሕ ሚስት ግን ከሁለቱም የከበረች ነች። 20 የወይን ጠጅና ሙዚቃ ልብን ያስደስታሉ፤ የጥበብ ፍቅር ግን ከሁሉም ይልቃል። 21 ዋሽንትና በገና መዝሙር ያጣፍጣሉ፤ ለዛ ያለው ድምፅ ግን ከሁሉም ይበልጣል። 22 ዐይን ግርማንና ውበትን ይናፍቃል፤ ከሁለቱም የተሻለው ግን የፀደይን ልምላሜ መመልከት ነው። 23 ወዳጅም ሆነ ጓደኛ ሲገኝ ያስደስታል፤ የባልና የሚስት መገኘት ግን የበለጠ ደስ ያሰኛል። 24 ወንድሞችና ደጋፊዎች ለመከራ ይደርሳሉ፤ ነገር ግን ምጽዋት ይበልጥ አዳኝ ነው። 25 ወርቅና ብር ጠንክረህ እንድትቆም ያደርጋሉ፤ ከሁለቱም የተሻለው ደግሞ መልካም ምክር ነው። 26 ብርና ኃይል ደንዳና ልብን ይፈጥራሉ፤ እግዚአብሔርን መፍራት ግን ከሁሉም ይልቃል፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ አንዳች አያጣም፤ የሌሎችንም ድጋፍ አይሻም። 27 እግዚአብሔርን መፍራት የምርቃት ገነት ነው፤ ከታላቅ ክብርም ይልቅ ያድናል። መቀላወጥ 28 ልጄ ሆይ! ከሌሎች በመቀላወጥ አትኑር፤ ቀላዋጭ ከመሆን መሞት ይመረጣል። 29 የሌላውን ሰው ማዕድ በመቀላወጥ የሚገፋ ሕይወት፥ ከቶውንም ሕይወት አይባልም፤ የሌሎች ምግብ ጉሮሮን ያሳድፋል፤ ጥበበኛ የሆነና መልካም አስተዳደግ ያለው ሰው ይህን አያደርግም። 30 የቀላዋጩ ቃል ሲሰሙት ይጣፍጣል፤ በሆዱ ውስጥ ግን እሳት ይነዳል። |