የእነርሱ ጣዖታት ግን የሰው እጅ ያበጃቸው፣ ብርና ወርቅ ናቸው።
አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፣
ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው፤ አያሸትቱም፤
እጅ አላቸው፤ አይዳስሱም፤ እግር አላቸው፤ አይሄዱም፤ በጕሮሯቸውም ድምፅ አይፈጥሩም።
እነዚህን የሚያበጁ፣ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።
አንሥተው በትከሻቸው ይሸከሙታል፤ እቦታው ያደርጉታል፤ በዚያም ይቆማል፤ ከዚያም ቦታ አይንቀሳቀስም፤ ማንም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይመልስም፤ ከጭንቀቱም አያድነውም።
እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው፤ በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም።
ጣዖቶቻቸው በኪያር ዕርሻ መካከል እንደ ቆመ ማስፈራርቾ ናቸው፤ የመናገር ችሎታ የላቸውም፤ መራመድም ስለማይችሉ፣ ተሸካሚ ያስፈልጋቸዋል፤ ጕዳት ማድረስም ሆነ፣ መልካምን ነገር ማድረግ ስለማይችሉ፣ አትፍሯቸው።”
ብፁዕ ነው፤ ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣ ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው፤
እርሱ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ የፈጠረ፣ ታማኝነቱም ለዘላለም የሆነ ነው፤
“የሰው እጅ የቀረጸው ጣዖት፣ ሐሰትንም የሚናገር ምስል ምን ፋይዳ አለው? ሠሪው በገዛ እጁ ሥራ ይታመናልና፣ መናገር የማይችሉ ጣዖታትን ይሠራልና።
እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ።
ኪዳኑንና ምስክርነቱን ለሚጠብቁ፣ የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ናቸው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣ ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ።
እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በተመረጠለት መንገድ ያስተምረዋል።
ዘመኑን በተድላ ደስታ ያሳልፋል፤ ዘሩም ምድርን ይወርሳል።
እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም፤ ኪዳኑንም ይገልጥላቸዋል።
ዐይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው፤ እግሮቼን ከወጥመድ የሚያላቅቃቸው እርሱ ነውና።
እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ እንደ መሆኔ፣ ወደ እኔ ተመለስ፤ ምሕረትም አድርግልኝ።
የልቤ መከራ በዝቷል፤ ከጭንቀቴ ገላግለኝ።
ጭንቀቴንና መከራዬን ተመልከት፤ ኀጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።
ጠላቶቼ እንዴት እንደ በዙ ተመልከት፤ እንዴት አምርረው እንደሚጠሉኝ እይ።
አምላኬ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ፤ እባክህ አታሳፍረኝ፤ ጠላቶቼም አይዘባነኑብኝ።
ለርዳታ በምትጮኺበት ጊዜ፣ የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች እስኪ ያድኑሽ! ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ይበትናቸዋል። እኔን መጠጊያው ያደረገ ሰው ግን፣ ምድሪቱን ይወርሳል፤ የተቀደሰ ተራራዬንም ገንዘቡ ያደርገዋል።”
ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔር እጁን ሲዘረጋ፣ ርዳታ ሰጪው ይሰናከላል፤ ተረጂውም ይወድቃል፤ ሁለቱም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።
ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የባሪያውንም ቃል የሚሰማ ማን ነው? ያ ሰው በጨለማ የሚሄድ ከሆነና፣ ብርሃንም ከሌለው፣ በእግዚአብሔር ስም ይታመን፤ በአምላኩም ይደገፍ።
በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ይህን የመሰለ ነው፤
ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፣ በራሳችን ብቃት ከእኛ ነው የምንለው አንዳች ነገር የለንም።
እግዚአብሔር፣ የቀባውን እንደሚያድን አሁን ዐወቅሁ። የማዳን ኀይል ባለው ቀኝ እጁ፣ ከተቀደሰው ሰማይ ይመልስለታል።
እነዚህ በሠረገላ፣ እነዚያ በፈረስ ይመካሉ፤ እኛ ግን ትምክሕታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ነው።
እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።
ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣
ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋራ የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።
መከራን የምቀበለውም ለዚሁ ነው፤ ሆኖም ያመንሁትን እርሱን ስለማውቅ አላፍርበትም፤ የሰጠሁትንም ዐደራ እስከዚያች ቀን ድረስ መጠበቅ እንደሚችል ተረድቻለሁ።
የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ትበረታላችሁ፤ እናንተ ግን ይህን አላደረጋችሁም፤
ወደ እስራኤል ቅዱስ ለማይመለከቱ፣ ከእግዚአብሔርም ርዳታን ለማይሹ፣ ነገር ግን፤ ለርዳታ ብለው ወደ ግብጽ ለሚወርዱ፣ በፈረሶች ለሚታመኑ፣ በሠረገሎቻቸው ብዛት፣ በፈረሶቻቸውም ታላቅ ብርታት ለሚመኩ ወዮላቸው!
“የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።
በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው።
“ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።
በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ።