መዝሙር 62 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 62 ለመዘምራን አለቃ፤ ለኤዶታም፤ የዳዊት መዝሙር። 1 ነፍሴ ዕረፍት የምታገኘው በእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ድነቴም የሚመጣልኝ ከርሱ ዘንድ ነው። 2 ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ ከቶም አልናወጥም። 3 ሰውን የምታጠቁት እስከ መቼ ነው? ይህን የዘመመ ግድግዳ፣ የተንጋደደ ዐጥር፣ ሁላችሁ ገፍታችሁ ልትጥሉት ትሻላችሁ? 4 ከታላቅ ክብሩ ሊያዋርዱት፣ ይህን አንድ ነገር ወጠኑ፤ ሐሰት ባለበት ነገር ደስ ይሰኛሉ፤ በአፋቸው ይመርቃሉ፤ በልባቸው ግን ይራገማሉ። ሴላ 5 ነፍሴ ሆይ፤ ዐርፈሽ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ፤ ተስፋዬ ከርሱ ዘንድ ነውና። 6 ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ እኔም አልናወጥም። 7 መዳኔና ክብሬ በእግዚአብሔር ነው፤ ብርቱ ዐለቴና መሸሸጊያዬ በእግዚአብሔር ነው። 8 ሰዎች ሆይ፤ ሁልጊዜ በርሱ ታመኑ፤ ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር መጠጊያችን ነውና። ሴላ 9 ከተናቀ ወገን መወለድ ከንቱ፣ ከከበረውም መወለድ ሐሰት ነው። በሚዛን ቢመዘኑ፣ የሰው ልጆች ሁሉ በአንድነት ከነፋስ የቀለሉ ናቸው። 10 በዝርፊያ አትታመኑ፤ በቅሚያም ተስፋ አታድርጉ፤ በዚህ ብትበለጽጉም፣ ልባችሁ ይህን አለኝታ አያድርግ። 11 እግዚአብሔር አንድ ነገር ተናገረ፤ እኔም ይህን ሁለት ጊዜ ሰማሁ፤ ኀይል የእግዚአብሔር ነው። 12 ጌታ ሆይ፤ ምሕረትም የአንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ፣ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.