Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 73 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ሦስተኛ መጽሐፍ ከመዝሙር 73–89 መዝሙር 73
የአሳፍ መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ልባቸው ንጹሕ ለሆነ፣ ለእስራኤል እንዴት ቸር ነው!

2 እኔ ግን እግሬ ሊሰናከል፣ አዳልጦኝም ልወድቅ ጥቂት ቀረኝ።

3 ክፉዎች ሲሳካላቸው አይቼ፣ በዐመፀኞች ቀንቼ ነበርና።

4 አንዳች ጣር የለባቸውም፤ ሰውነታቸውም ጤናማና የተደላደለ ነው።

5 በሰዎች የሚደርሰው ጣጣ አይደርስባቸውም፤ እንደ ማንኛውም ሰው መከራ አያገኛቸውም።

6 ስለዚህ ትዕቢት የዐንገት ጌጣቸው ነው፤ ዐመፅንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈዋል።

7 የሠባ ዐይናቸው ይጕረጠረጣል፤ ልባቸውም በከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይፈስሳል።

8 በፌዝና በክፋት ይናገራሉ፤ ቀና ቀና ብለውም በዐመፅ ይዝታሉ።

9 አፋቸውን በሰማይ ላይ ያላቅቃሉ፤ አንደበታቸውም ምድርን ያካልላል።

10 ስለዚህ ሕዝቡ ወደ እነርሱ ይነጕዳል፤ ውሃቸውንም በገፍ ይጠጣሉ።

11 “ለመሆኑ እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ ዕውቀት አለ?” ይላሉ።

12 እንግዲህ፣ ክፉዎች ይህን ይመስላሉ፤ ሁልጊዜ ግድ የለሽና ሀብት በሀብት ናቸው።

13 ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤ እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሯል!

14 ቀኑን ሙሉ ተቀሠፍሁ፤ ጧት ጧትም ተቀጣሁ።

15 “እኔ እንደዚህ እናገራለሁ” ብልማ ኖሮ፣ የልጆችህን ትውልድ በከዳሁ ነበር።

16 ይህን ነገር ለመረዳት በሞከርሁ ጊዜ፣ አድካሚ ተግባር መስሎ ታየኝ።

17 ይኸውም ወደ አምላክ መቅደስ እስክገባ፣ መጨረሻቸውንም እስካይ ድረስ ነበር።

18 በርግጥ በሚያዳልጥ ስፍራ አስቀመጥሃቸው፤ ወደ ጥፋትም አወረድሃቸው።

19 እንዴት ፈጥነው በቅጽበት ጠፉ! በድንጋጤ ፈጽመው ወደሙ።

20 ሰው ከሕልሙ ሲነቃ እንደሚሆነው፣ ጌታ ሆይ፤ አንተም በምትነሣበት ጊዜ፣ እንደ ቅዠት ከንቱ ታደርጋቸዋለህ።

21 ነፍሴ በተማረረች ጊዜ፣ ልቤም በተቀሠፈ ጊዜ፣

22 ደነዝና አላዋቂ ሆንሁ፤ በፊትህም እንደ እንስሳ ሆንሁ።

23 ይህም ሆኖ ዘወትር ከአንተ ጋራ ነኝ፤ አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል።

24 በምክርህ መራኸኝ፤ ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ።

25 በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም።

26 ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣ የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው።

27 እነሆ፤ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና፤ አንተ የሚያመነዝሩትን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ።

28 ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ ጌታ እግዚአብሔርን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ፤ ስለ ሥራህም ሁሉ እናገር ዘንድ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች