ኤርምያስ 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “የይሁዳ ኀጢአት በብረት ብርዕ፣ በሾለ የአልማዝ ጫፍ፣ ተጽፏል፤ በልባቸው ጽላት፣ በመሠዊያቸውም ቀንዶች ላይ ተቀርጿል። 2 ልጆቻቸው እንኳ ሳይቀሩ፣ በለመለሙ ዛፎች ሥር፣ ከፍ ባሉ ኰረብቶችም ላይ ያሉትን፣ መሠዊያቸውንና አሼራ የተባለችውን ጣዖት ምስል ያስባሉ። 3 በአገርህ ሁሉ ከተፈጸመው ኀጢአት የተነሣ፣ በምድሪቱ ያለህ ተራራዬ፣ ሀብትህንና ንብረትህን ሁሉ፣ መስገጃ ኰረብቶችህንም ጭምር፣ ለብዝበዛ አደርገዋለሁ። 4 በገዛ ጥፋትህ፣ የሰጠሁህን ርስት ታጣለህ፤ በማታውቀውም ምድር፣ ለጠላቶችህ ባሪያ አደርግሃለሁ፤ ለዘላለም የሚነድደውን፣ የቍጣዬን እሳት ጭረሃልና።” 5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰው የሚታመን፣ በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣ ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው። 6 በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፤ መልካም ነገር ሲመጣ አያይም፤ ሰው በሌለበት በጨው ምድር፣ በምድረ በዳ በደረቅ ስፍራ ይቀመጣል። 7 “ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። 8 በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ ቅጠሉም ዘወትር እንደ ለመለመ ነው፤ በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።” 9 የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል? 10 “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣ ልብን እመረምራለሁ፤ የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።” 11 ሀብትን በግፍ የሚያከማች ሰው፣ ያልፈለፈለችውን ጫጩት እንደምትታቀፍ ቆቅ ነው፤ በዕድሜው አጋማሽ ትቶት ይሄዳል፤ በመጨረሻም ሞኝነቱ ይረጋገጣል። 12 የመቅደሳችን ስፍራ፣ ከጥንት ጀምሮ ከፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው። 13 የእስራኤል ተስፋ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጥለውህ የሚሄዱ ሁሉ ያፍራሉ፤ ፊታቸውን ከአንተ የሚመልሱ በምድር ውስጥ ይጻፋሉ፤ የሕይወትን ውሃ ምንጭ፣ እግዚአብሔርን ትተዋልና። 14 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈውሰኝ፤ እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና። 15 እነርሱ ደጋግመው፣ “የእግዚአብሔር ቃል የት አለ? እስኪ አሁን ይፈጸም!” ይሉኛል። 16 እረኛ ሆኜ አንተን ከማገልገል ወደ ኋላ አላልሁም፤ ክፉ ቀን እንዳልተመኘሁ ታውቃለህ፤ ከአንደበቴ የሚወጣውም በፊትህ ግልጽ ነው። 17 አስደንጋጭ አትሁንብኝ፤ በመከራ ቀን መሸሸጊያዬ አንተ ነህ። 18 አሳዳጆቼ ይፈሩ፤ እኔን ግን ከዕፍረት ጠብቀኝ፤ እነርሱ ይደንግጡ፤ እኔን ግን ከድንጋጤ ሰውረኝ፤ ክፉ ቀን አምጣባቸው፤ በዕጥፍ ድርብ ጥፋት አጥፋቸው። ሰንበትን ማክበር 19 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ሄደህ የይሁዳ ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ በር በሌሎቹም የኢየሩሳሌም በሮች ሁሉ ቁም፤ 20 እንዲህም በላቸው፤ ‘በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ነገሥታት ሆይ፤ የይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳታስገቡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 22 አባቶቻችሁን እንዳዘዝኋቸው ሰንበትን አክብሩ እንጂ በሰንበት ቀን ከየቤታችሁ ሸክም ይዛችሁ አትውጡ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ።” 23 እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም ዐንገታቸውን አደነደኑ። 24 ነገር ግን በጥንቃቄ ብትታዘዙኝ ይላል እግዚአብሔር፤ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ይዛችሁ ባትገቡ፣ የሰንበትንም ቀን ምንም ሳትሠሩ ብትቀድሱት፣ 25 በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መኳንንታቸው በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ በፈረሶችና በሠረገሎች ተቀምጠው በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ታጅበው ይመጣሉ፤ ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች። 26 ሰዎች ከይሁዳ ከተሞች፣ ከኢየሩሳሌም ዙሪያ፣ ከብንያምም አገር፣ ከቈላውና ከደጋው አገር እንዲሁም ከኔጌብ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ ዕጣንና የምስጋና መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ። 27 ነገር ግን የሰንበትን ቀን ሳትቀድሱ፣ በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች በመግባት ትእዛዜን ብትጥሱ፣ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ ምሽጎቿን የሚበላ፣ የማይጠፋ እሳት እጭራለሁ።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.