መዝሙር 31 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 31 31፥1-4 ተጓ ምብ – መዝ 71፥1-3 ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መጠጊያ አደረግሁ፤ ከቶም አልፈር፤ በጽድቅህም ታደገኝ። 2 ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ ፈጥነህ አድነኝ፤ መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤ ታድነኝም ዘንድ ምሽግ ሁነኝ። 3 አንተ ዐለቴና መጠጊያዬ ነህና፣ ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤ መንገዱንም ጠቍመኝ። 4 አንተ መጠጊያዬ ነህና፣ በስውር ከተዘረጋብኝ ወጥመድ አውጣኝ። 5 መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ፤ እግዚአብሔር የእውነት አምላክ ሆይ፤ አንተ ተቤዠኝ። 6 ለከንቱ ጣዖታት ስፍራ የሚሰጡትን ጠላሁ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ። 7 በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ መከራዬን አይተሃልና፤ የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል። 8 ለጠላት አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን እግሮቼን ሰፊ ቦታ ላይ አቆምሃቸው። 9 እግዚአብሔር ሆይ፤ በመከራ ውስጥ ነኝና ማረኝ፤ ዐይኖቼ በሐዘን ደክመዋል፤ ነፍስና ሥጋዬም ዝለዋል። 10 ሕይወቴ በመጨነቅ፣ ዕድሜዬም በመቃተት ዐለቀ፤ ከመከራዬ የተነሣ ጕልበት ከዳኝ፤ ዐጥንቴም በውስጤ ሟሟ። 11 ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ፣ ለጎረቤቶቼ መዘባበቻ፣ ለወዳጆቼ መሣለቂያ ሆኛለሁ፤ መንገድ ላይ የሚያገኙኝም ይሸሹኛል። 12 እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤ እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃም ተቈጠርሁ። 13 የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁና፤ ዙሪያው ሁሉ ሽብር አለ፤ በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ፣ ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ። 14 እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም። 15 ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤ ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤ ከሚያሳድዱኝም አድነኝ። 16 ፊትህን በአገልጋይህ ላይ አብራ፤ በምሕረትህም አድነኝ። 17 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁና አልፈር፤ ክፉዎች ግን ይፈሩ፤ ሲኦል ገብተውም ጸጥ ይበሉ። 18 በጻድቁ ላይ በእብሪት የሚናገሩ፣ ትዕቢትንና ንቀትን የተሞሉ፣ ዋሾ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ። 19 በሰዎች ልጆች ፊት፣ ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣ መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣ በጎነትህ ምንኛ በዛች! 20 ከሰዎች ሤራ፣ በማደሪያህ ውስጥ ትሸሽጋቸዋለህ፤ ከአንደበት ጭቅጭቅም፣ በድንኳንህ ውስጥ ትከልላቸዋለህ። 21 በተከበበች ከተማ ውስጥ፣ የሚያስደንቅ ምሕረቱን ያሳየኝ፣ እግዚአብሔር ይባረክ። 22 እኔ በደነገጥሁ ጊዜ፣ “ከዐይንህ ፊት ተወግጃለሁ” አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ ስጮኽ፣ የልመናዬን ቃል ሰማህ። 23 እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት! እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤ ትዕቢተኞችን ግን ፈጽሞ ይበቀላቸዋል። 24 እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤ በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.