በወደዷቸውና በአገለገሏቸው እንዲሁም በተከተሏቸው፣ ባማከሯቸውና ባመለኳቸው በፀሓይ፣ በጨረቃና በሰማያት ከዋክብት ሁሉ ፊት ይሰጣል፤ አይሰበሰብም ወይም አይቀበርም፤ ነገር ግን እንደ ተጣለ ጕድፍ በምድር ላይ ይበተናል።
ኤልያስም በሕዝቡ ፊት ቀርቦ፣ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አለ። ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሱም።
እኔን ትተውኝ፣ ይህን ስፍራ የባዕድ አማልክት ቦታ አድርገውታልና። እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው፣ የይሁዳ ነገሥታትም ለማያውቋቸው አማልክት ሠውተዋል፤ ይህንም ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታል፤ እኔም ያላዘዝኋቸውን፣ ያልተናገርኋቸውን፣ ፈጽሞም ያላሰብሁትን፣ ወንዶች ልጆቻቸውን በእሳት ሊሠዉለት ለበኣል መስገጃ ኰረብቶች ሠርተዋል።
ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፤ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን አማልክት ተከተሉ፤ ሰገዱላቸውም። እግዚአብሔርንም አስቈጡት፤
እነርሱ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን? ለሰማይዋ ንግሥት ቂጣ ሊጋግሩ፣ ልጆች ዕንጨት ይለቅማሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶችም ሊጥ ያቦካሉ፤ ሊያስቈጡኝም ለሌሎች አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀርባሉ።
የሴሰኝነታችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ፤ ጣዖት በማምለክ ለፈጸማችሁት ኀጢአት ቅጣት ትሸከማላችሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”
“ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብጽንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብጽ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር።
በጣዖቶቻቸው፣ በአስጸያፊ ምስሎቻቸው ወይም በማንኛውም ኀጢአት ራሳቸውን አያረክሱም፤ ነገር ግን እኔን በመተው ከሠሩት ኀጢአት ሁሉ አድናቸዋለሁ፤ አነጻቸዋለሁም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።
ስለዚህ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ወዮ እነዚህ ሕዝብ የሠሩት ምን ዐይነት የከፋ ኀጢአት ነው! ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት ሠሩ።
በባሉጥ ዛፎች መካከል፣ ቅጠሉ በተንዠረገገ ዛፍ ሥር በዝሙት የምትቃጠሉ፣ በሸለቆዎች፣ በዐለት ስንጣቂዎችም ውስጥ ልጆቻችሁን የምትሠዉ አይደላችሁምን?
ከተማዪቱን የሚወጓት ባቢሎናውያን ወደ ውስጥ ይገባሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል፤ ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቡ በየሰገነቱ ላይ ለበኣል ያጠኑባቸውንና ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀረቡባቸውን ቤቶች ጭምር ያነድዳሉ።
“ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የማትሰሙኝ ከሆነ፣ እያንዳንዳችሁ ሂዱና ለጣዖቶቻችሁ ስገዱ! ነገር ግን በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን ከእንግዲህ አታረክሱም።
በእነዚህ መቅሠፍቶች ሳይገደሉ የቀሩት ሰዎች አሁንም ከእጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትን እንዲሁም ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን፣ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከናስ፣ ከድንጋይና ከዕንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች ማምለክ አልተዉም፤
አሁንም ኀጢአትን መሥራት አበዙ፤ ብራቸውን አቅልጠው ለራሳቸው ጣዖት ሠሩ፣ በጥበብ የተሠሩ ምስሎችን አበጁ፤ ሁሉም የእጅ ጥበብ ባለሙያ ናቸው። ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ተብሏል፤ “ሰውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤ የጥጃ ጣዖቶችንም ይስማሉ!”
ይሁዳ ሆይ፤ የአማልክትህ ቍጥር የከተሞችህን ብዛት ያህል ነው፤ አሳፋሪ ለሆነው ጣዖት፣ ለበኣል ማጠኛ የሠራችኋቸው መሠዊያዎቻችሁ ብዛት የኢየሩሳሌምን መንገዶች ያህል ነው።’
እንዲህም ስል በጠቅላላው ከዚህ ዓለም ሴሰኞች ወይም ስግብግቦችና ቀማኞች ወይም ከጣዖት አምላኪዎች ጋራ አትተባበሩ ለማለት አይደለም፤ እንደዚያማ ቢሆን ከዚህ ዓለም ጨርሶ መለየት ያስፈልጋችሁ ነበር።
ከአንተ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ አንተ የከፋ ሥራ ሠራህ፤ ለራስህም ከቀለጠ ብረት ሌሎች አማልክትን ሠራህ፤ ቍጣዬን አነሣሣህ፤ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ።
በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሚገኙ ኰረብቶች ላይ ዕጣን እንዲያጥኑ የይሁዳ ነገሥታት የሾሟቸውን የጣዖት ካህናት አባረረ እንዲሁም ለበኣል፣ ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት የሚያጥኑትን አስወገደ።
ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋራ የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤ እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዝዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤ እግዚአብሔር እንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።
እግዚአብሔር በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፤ “ከዳተኛዪቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ከፍ ወዳለው ኰረብታ ሁሉ ወጥታ፣ ወደ ለመለመው ዛፍ ሥር ሁሉ ሄዳ በዚያ አመነዘረች።
በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ።
“ነገር ግን እግዚአብሔርን ለተዋችሁት ለእናንተ፣ የተቀደሰ ተራራዬን ለረሳችሁት፣ ‘ዕጣ ፈንታ’ ለተባለ ጣዖት ቦታ ላዘጋጃችሁት፣ ‘ዕድል’ ለተባለም ጣዖት ድብልቅ የወይን ጠጅ በዋንጫ ለሞላችሁት፣
እኔም ገብቼ አየሁ፤ እነሆ የሚሳቡ ፍጥረታትና የርኩሳን አራዊት ዐይነት ሁሉ፣ የእስራኤልም ቤት ጣዖታት ሁሉ ዙሪያውን በግንቡ ላይ ተቀርጸው ነበር።
ለበኣል አማልክት ዕጣን ስላጠነችባቸው ቀናት እቀጣታለሁ፤ በጌጣጌጥና በቀለበቶች ራሷን አስጊጣለች፤ ውሽሞቿንም ተከትላ ሄዳለች፤ እኔን ግን ረስታለች” ይላል እግዚአብሔር።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነዚህ ነቢያት የሚተነብዩላችሁን አትስሙ፤ በባዶ ተስፋ ይሞሏችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ ይናገራሉ።
“በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ።
ከመዝጊያሽና ከመቃንሽ ጀርባ፣ የጣዖት ምስሎችሽን ሰቀልሽ፤ እኔን ትተሽ መኝታሽን ገላለጥሽ፤ በላይም ወጥተሽ በጣም ገለጥሽው፤ መኝታቸውን ከወደድሽላቸው ጋራ ስምምነት አደረግሽ፤ ዕርቃናቸውንም አየሽ።
ሕዝቡ፣ ‘እግዚአብሔር አምላካችን ይህን ሁሉ ነገር ለምን አደረገብን?’ ብለው ቢጠይቁ፣ ‘እኔን፣ እንደ ተዋችሁኝና በራሳችሁ ምድር ባዕዳን አማልክትን እንዳገለገላችሁ፣ እንደዚሁ የእናንተ ባልሆነ ምድር ባዕዳንን ታገለግላላችሁ’ ትላቸዋለህ።
እናንተንም፣ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ’ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።”
የገዛ ወንድ ልጁን በእሳት ሠዋ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቍጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።
የያዕቆብ ቤት የሆነውን ሕዝብህን ትተሃል፤ እነርሱ በምሥራቅ ሰዎች ከንቱ አምልኮ ተሞልተዋልና፤ እንደ ፍልስጥኤማውያን ያሟርታሉ፤ ከባዕዳን ጋራ አገና ይማታሉ።
ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኩሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”
በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ወግና በዚህ ዓለም መሠረታዊ መንፈሳዊ ኀይሎች ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።
“እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም።
ለርዳታ በምትጮኺበት ጊዜ፣ የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች እስኪ ያድኑሽ! ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ይበትናቸዋል። እኔን መጠጊያው ያደረገ ሰው ግን፣ ምድሪቱን ይወርሳል፤ የተቀደሰ ተራራዬንም ገንዘቡ ያደርገዋል።”
በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሟርተኛ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል፣ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነውና። ከእነዚህ አስጸያፊ ልምዶች የተነሣም አምላክህ እግዚአብሔር እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል።
ሰዎች፣ የሚያነበንቡትንና የሚያንሾካሽኩትን ሟርተኞችንና መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ ቢሏችሁ፣ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን? በሕያዋን ምትክ ሙታንን መጠየቅ ለምን አስፈለገ?
ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።”
እግዚአብሔር በኮሬብ ተራራ ላይ በእሳት ውስጥ በተናገራችሁ ቀን ምንም ዐይነት መልክ ከቶ አላያችሁም፤ ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ይኸውም እንዳትረክሱ፣ በወንድ ወይም በሴት መልክ በማንኛውም ዐይነት ምስል የተቀረጸ ጣዖት ለራሳችሁ እንዳታበጁ፣
የእነርሱ ጣዖታት ግን የሰው እጅ ያበጃቸው፣ ብርና ወርቅ ናቸው። አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፣ ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው፤ አያሸትቱም፤ እጅ አላቸው፤ አይዳስሱም፤ እግር አላቸው፤ አይሄዱም፤ በጕሮሯቸውም ድምፅ አይፈጥሩም።
የተቀበልሽው ምክር ሁሉ ድካም ብቻ ሆኖ አስቀርቶሻል! እነዚያ ከወር እስከ ወር ከዋክብትን አንጋጦ በማየት የሚተነብዩ፣ ኮከብ ቈጣሪዎች እስኪ ይምጡ፤ ከሚደርስብሽም ነገር እስኪ ያድኑሽ። እነሆ፣ እነርሱ ገለባ ናቸው፤ እሳት ይበላቸዋል፤ ከነበልባሉ ወላፈን የተነሣ፣ ራሳቸውን ማዳን አይችሉም። ሰው የሚሞቀው ፍም አይኖርም፤ ተቀምጠው የሚሞቁትም እሳት የለም።
ራእያቸው ሐሰት፣ ጥንቈላቸው ውሸት ነው፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ይላሉ፤ ይህም ሆኖ የተናገሩት ይፈጸማል ብለው ይጠብቃሉ።
እናደርጋለን ያልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ አባቶቻችን፣ ነገሥታታችንና ባለሥልጣኖቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም ለሰማይዋ ንግሥት እናጥናለን፤ የመጠጥ ቍርባን እናፈስስላታለን። በዚያ ጊዜ የተትረፈረፈ ምግብ ነበረን፤ በመልካም ሁኔታ እንገኝ ነበር እንጂ ምንም ክፉ ነገር አልገጠመንም። ነገር ግን ለሰማይዋ ንግሥት ማጠንና የመጠጥ ቍርባን ማፍሰስ ከተውን ወዲህ ሁሉን ነገር ዐጥተናል፤ በሰይፍና በራብም እያለቅን ነው።”
“እያንዳንዳቸው ጅሎችና ዕውቀት የለሽ ናቸው፤ የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው ጣዖት ዐፍሯል፤ የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤ እስትንፋስም የላቸውም።
እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋራ ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋራ ታነጻጽሩታላችሁ? የተቀረጸውንማ ምስል የእጅ ጥበብ ባለሙያ ይቀርጸዋል፤ ወርቅ አንጥረኛም በወርቅ ይለብጠዋል፤ የብር ሰንሰለትም ያበጅለታል። ለኢየሩሳሌም አለዝባችሁ ንገሯት፤ ዐውጁላትም፤ በባርነት ያገለገለችበት ዘመን አብቅቷል፤ የኀጢአቷም ዋጋ ተከፍሏል፤ ስለ ኀጢአቷ ሁሉ ከእግዚአብሔር እጅ ሁለት ዕጥፍ ተቀብላለች። እንዲህ ያለውን መባ ማቅረብ የማይችል ምስኪን ድኻ፣ የማይነቅዝ ዕንጨት ይመርጣል፤ የማይወድቅ ምስልን ለማቆምም፣ ታዋቂ የእጅ ጥበብ ባለሙያ ይፈልጋል።
የአሕዛብ ጣዖታት ከብርና ከወርቅ የተሠሩ፣ የሰው እጅ ያበጃቸው ናቸው። አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፤ ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ በአፋቸውም እስትንፋስ የለም። እነዚህን የሚያበጁ፣ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።
የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ ያሰናክልሃል። አስጸያፊ ነገርን ወደ ቤትህ ወይም ወደ ራስህ አታምጣ፤ አለዚያ አንተም እንደ እርሱ ለጥፋት ትዳረጋለህ፤ ፈጽመህ ጥላው፤ ተጸየፈውም፤ ለጥፋት የተለየ ነውና።
ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፣ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያደምጣሉ፤ አንተ ግን ይህን እንድታደርግ አምላክህ እግዚአብሔር አልፈቀደልህም።
እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት፣ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደ ሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።
“የሰው እጅ የቀረጸው ጣዖት፣ ሐሰትንም የሚናገር ምስል ምን ፋይዳ አለው? ሠሪው በገዛ እጁ ሥራ ይታመናልና፣ መናገር የማይችሉ ጣዖታትን ይሠራልና።
እነዚህ ከሰይፍ የተረፉት፣ ከእኔ ዘወር ባለ አመንዝራ ልባቸውና ጣዖትን በተከተለ አመንዝራ ዐይናቸው የቱን ያህል እንዳሳዘኑኝ፤ በአሕዛብ ምድር ሆነው ያስታውሱኛል፤ ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ርኩስ ተግባር ሁሉ የተነሣም ራሳቸውን ይጸየፋሉ።
ብርታቴና ምሽጌ፣ በመከራ ቀን መጠጊያዬ የሆንህ እግዚአብሔር ሆይ፤ አሕዛብ ከምድር ዳርቻ፣ ወደ አንተ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “አባቶቻችን ለአንዳች ነገር ያልረቧቸውን ከንቱ ጣዖቶች፣ የሐሰት አማልክትን ወረሱ።