Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 94 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 94

1 የበቀል አምላክ፣ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤ የበቀል አምላክ ሆይ፤ ደምቀህ ተገለጥ።

2 አንተ የምድር ዳኛ ሆይ፤ ተነሥ፤ ለትዕቢተኞች የእጃቸውን ስጣቸው።

3 ክፉዎች እስከ መቼ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎች እስከ መቼ ይፈነጫሉ?

4 የእብሪት ቃላት ያዥጐደጕዳሉ፤ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ጕራ ይነዛሉ።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አደቀቁ፤ ርስትህንም አስጨነቁ።

6 መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤ የድኻ አደጉንም ነፍስ አጠፉ።

7 እነርሱም “እግዚአብሔር አያይም፤ የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም” አሉ።

8 እናንተ በሕዝቡ መካከል ያላችሁ ደነዞች፤ ልብ በሉ፤ እናንተ ሞኞች፤ ጥበበኞች የምትሆኑት መቼ ነው?

9 ጆሮን የተከለው እርሱ አይሰማምን? ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?

10 ሕዝቦችን በተግሣጽ ወደ መንገድ የሚመልስ፣ ዕውቀትንስ ለሰው ልጆች የሚያስተምር አይቀጣምን?

11 እግዚአብሔር የሰው ሐሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል።

12 ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የምትገሥጸው፣ ከሕግህም የምታስተምረው ሰው፤

13 ለኀጢአተኞች ጕድጓድ እስኪማስላቸው ድረስ፣ እርሱን ከመከራ ታሳርፈዋለህ።

14 እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፤ ርስቱንም አይተውም።

15 ፍርድ ተመልሶ በጽድቅ አሠራር ላይ ይመሠረታል፤ ልባቸውም ቀና የሆነ ሁሉ ይከተሉታል።

16 ክፉዎችን የሚቋቋምልኝ ማን ነው? ከክፉ አድራጊዎችስ ጋራ የሚሟገትልኝ ማን ነው?

17 እግዚአብሔር ረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣ ነፍሴ ወደ ዝምታው ዓለም ፈጥና በወረደች ነበር።

18 እኔ፣ “እግሬ አዳለጠኝ” ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ።

19 የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።

20 ዐመፃን ሕጋዊ የሚያደርግ፣ የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋራ ሊያብር ይችላልን?

21 በጻድቁ ላይ ተሰልፈው ይወጣሉ፤ በንጹሑም ላይ ሞት ይፈርዳሉ።

22 ለእኔ ግን እግዚአብሔር ምሽግ፣ አምላኬም መጠጊያ ዐለት ሆኖኛል።

23 በደላቸውን ወደ ራሳቸው ይመልሳል፤ በክፋታቸውም ያጠፋቸዋል፤ እግዚአብሔር አምላካችን ይደመስሳቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች