ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ የውስጥ ሰውነቴም ሁሉ ቅዱስ ስሙን ባርኪ።
እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።
ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት።
ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ።
አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል።
እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።
ሰው እኮ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ ያቈጠቍጣል፤
ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ድራሹ ይጠፋል፤ ምልክቱም በቦታው አይገኝም።
የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤
ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣ ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጕት ላይ ይሆናል።
እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቷል፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ ውለታውንም ሁሉ አትርሺ፤
ሁልጊዜ በልግስና መስጠት እንድትችሉ በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል፤ ልግስናችሁም በእኛ በኩል የሚደርሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት ይሆናቸዋል።
የአባቶቼ አምላክ ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ፤ አከብርሃለሁም፤ ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛልና፤ ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤ የንጉሡን ሕልም አሳውቀኸናል።”
ወንድሞች ሆይ፤ እምነታችሁ በየጊዜው እያደገ በመሄዱና የእርስ በርስ ፍቅራችሁም እየጨመረ በመምጣቱ፣ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሚገባ ማመስገን አለብን።
እንዲሁም “ፍቅሩ ለዘላለም ነውና” እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና እንዲያቀርቡ ኤማንና ኤዶታም እንዲሁም ተመርጠውና ስማቸው ተመዝግቦ የተመደቡ ሌሎችም ዐብረዋቸው ነበሩ።
በዚያ ቀን እንዲህ ትላላችሁ፤ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ያደረገውንም በአሕዛብ መካከል አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱንም ዐውጁ።
ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ሳይሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ስለ ተቀበላችሁ፣ ደግሞም እውነት ነው፤ እግዚአብሔርን ያለ ማቋረጥ እናመሰግናለን፤ ይኸውም ቃል በእናንተ ዘንድ የሚሠራ ነው።
ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ በድል አድራጊነት እያዞረ ለሚመራን፣ የዕውቀቱንም መዐዛ በእኛ አማካይነት በየስፍራው ለሚገልጥ አምላክ ምስጋና ይሁን፤
እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤
እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቷልና፤ የተራበችውንም ነፍስ በበጎ ነገር አጥግቧል።
“የመዳናችን አምላክ ሆይ አድነን፤ ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣ በምስጋናህም እንድንከብር ሰብስበን፤ ከአሕዛብም መካከል ታደገን” ብላችሁ ጩኹ።
እኔም የይሁዳን መሪዎች በቅጥሩ ግንብ ዐናት ላይ እንዲወጡ አደረግሁ፤ ደግሞም ምስጋና እንዲያቀርቡ ሁለት ታላላቅ የመዘምራን ቡድን መደብሁ። አንዱ በቅጥሩ ግንብ ዐናት በስተቀኝ በኩል ቈሻሻ መጣያ በር ወደሚባለው ሄደ።
መለከት ነፊዎችና ዘማሪዎችም በአንድነት አንድ ድምፅ ሆነው ለእግዚአብሔር ውዳሴና ምስጋና አቀረቡ፤ በመለከት፣ በጸናጽልና በሌሎች መሣሪያዎች ታጅበውም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እግዚአብሔርን እያወደሱ፣ “እርሱ ቸር ነው፣ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” እያሉ ዘመሩ። ከዚያም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በደመና ተሞላ።
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን! እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባሪያ ስሆን፣ በኀጢአተኛ ተፈጥሮዬ ግን ለኀጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።
ዳንኤልም ዐዋጁ እንደ ወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹ በኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ፤ አምላኩንም አመሰገነ።
ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደ አዲስ ስለ እኔ ማሰብ በመጀመራችሁ፣ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በርግጥ በተግባር ለመግለጽ ዕድሉ አልነበራችሁም እንጂ ማሰቡንስ ታስቡልኝ ነበር።
አንተ አምላኬ ነህ፤ አመሰግንሃለሁ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።
ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው፣ እንዲህ የሚያደርገው ለጌታ ብሎ ነው፤ ሥጋ የሚበላውም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባልና። የማይበላም ለጌታ ሲል አይበላም፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ያቀርባል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አወድሳለሁ፤ አስቀድሞ የታሰበውን፣ ድንቅ ነገር፣ በፍጹም ታማኝነት አድርገሃልና።
የሐሤትና የደስታ ድምፅ፣ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ እንዲሁም፣ “ ‘ “እግዚአብሔር ቸር ነውና፤ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚል የምስጋናን መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡ ሰዎች ድምፅ ይሰማል፤ የምድሪቱን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ እመልሳለሁና፤’ ይላል እግዚአብሔር።
በዚያ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ።