1 ተሰሎንቄ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየጳውሎስ አገልግሎት በተሰሎንቄ 1 ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ የመጣነው ለከንቱ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 2 እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ መከራ ተቀብለን ተንገላታን፤ ነገር ግን ብርቱ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ፣ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን። 3 የምናቀርበው ልመና ከስሕተት ወይም ከክፉ ዐላማ ወይም እናንተን ለማታለል ከመፈለግ የመነጨ አይደለም። 4 ነገር ግን ወንጌልን በዐደራ ለመቀበል እግዚአብሔር ብቁ አድርጎ እንደ ቈጠራቸው ሰዎች ሆነን እንናገራለን። ይህንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ደስ ለማሠኘት ብለን አይደለም። 5 የሽንገላ ቃል ከቶ እንዳልተናገርን ወይም ሥሥትን ለመሸፈን ብለን አስመሳዮች እንዳልሆንን ታውቃላችሁ፤ ለዚህም እግዚአብሔር ምስክራችን ነው። 6 ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም፣ ከሰው የሚገኝ ክብር አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ሸክም በሆንንባችሁ ነበር፤ 7 ነገር ግን እናት ልጇን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በየዋህነት ተመላለስን። 8 የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ። 9 ወንድሞች ሆይ፤ ጥረታችንንና ድካማችንን ታስታውሳላችሁ፤ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እየሠራን የእግዚአብሔርን ወንጌል ሰበክንላችሁ። 10 በእናንተ በምታምኑት መካከል ሳለን እንዴት በቅድስና፣ በጽድቅ እንዲሁም ያለ ነቀፋ ሆነን እንደ ኖርን እናንተም እግዚአብሔርም ምስክሮች ናችሁ። 11 አባት ለገዛ ልጆቹ እንደሚሆን እኛም ለእያንዳንዳችሁ የቱን ያህል እንደ ሆንን ታውቃላችሁና፤ 12 ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትኖሩ ዘንድ አበረታታናችሁ፤ አጽናናናችሁ፤ አጥብቀንም ለመንናችሁ። 13 ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ሳይሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ስለ ተቀበላችሁ፣ ደግሞም እውነት ነው፤ እግዚአብሔርን ያለ ማቋረጥ እናመሰግናለን፤ ይኸውም ቃል በእናንተ ዘንድ የሚሠራ ነው። 14 ወንድሞች ሆይ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን በይሁዳ የሚገኙትን የእግዚአብሔርን አብያተ ክርስቲያናት መስላችኋል፤ እነዚያ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፣ እናንተም ከገዛ ወገኖቻችሁ መከራን ተቀብላችኋል። 15 እነርሱ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም አሳደዱን፤ እግዚአብሔርንም ደስ አላሠኙትም፤ የሰውም ሁሉ ፀር ሆኑ፤ 16 ይኸውም ይድኑ ዘንድ ለአሕዛብ እንዳንናገር ለመከልከል ነው፤ በዚህ ሁኔታ ኀጢአታቸውን ሁልጊዜ በራሳቸው ላይ እስከ መጨረሻው እያከማቹ ይሄዳሉ። ቍጣውም በእነርሱ ላይ ያለ ልክ መጥቷል። ጳውሎስ የተሰሎንቄን ሰዎች ለማየት የነበረው ናፍቆት 17 ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፤ እኛ በልባችን ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ብንለይም፣ ለእናንተ ካለን ታላቅ ናፍቆት የተነሣ ፊታችሁን ለማየት ብርቱ ጥረት አደረግን። 18 ወደ እናንተ ለመምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን አዘገየን። 19 ጌታችን ኢየሱስ ሲመጣ በርሱ ፊት ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም አክሊላችን ማን ነው? እናንተ አይደላችሁምን? 20 በርግጥ እናንተ ክብራችንም ደስታችንም ናችሁ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.