መዝሙር 92 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 92 በሰንበት ቀን የሚዘመር መዝሙር፤ ማሕሌት። 1 እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፤ ልዑል ሆይ፤ ለስምህ መዘመር ጥሩ ነው፤ 2 ምሕረትህን በማለዳ፣ ታማኝነትህንም በሌሊት ማወጅ መልካም ነው፤ 3 ዐሥር አውታር ባለው በገና፣ በመሰንቆም ቅኝት ታጅቦ ማወጅ ጥሩ ነው። 4 እግዚአብሔር ሆይ፤ በሥራህ ስለ ተደሰትሁ፣ ስለ እጅህ ሥራ በደስታ እዘምራለሁ። 5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ታላቅ ነው! ሐሳብህስ ምን ያህል ጥልቅ ነው! 6 ደነዝ ሰው ይህን አያውቅም፤ ሞኝም አያስተውለውም። 7 ክፉዎች እንደ ሣር ቢበቅሉ፣ ክፉ አድራጊዎች ቢለመልሙ፣ ለዘላለሙ ይጠፋሉ። 8 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ለዘላለም ልዑል ነህ። 9 ጠላቶችህ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፤ ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ይበተናሉ። 10 የእኔን ቀንድ ግን እንደ አውራሪስ ቀንድ ከፍ ከፍ አደረግኸው፤ በለጋ ዘይትም አረሰረስኸኝ። 11 ዐይኖቼ የባላንጦቼን ውድቀት አዩ፤ ጆሮዎቼም የክፉ ጠላቶቼን ድቀት ሰሙ። 12 ጻድቃን እንደ ዘንባባ ይንሰራፋሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይንዠረገጋሉ። 13 በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል፤ በአምላካችንም አደባባይ ይንሰራፋሉ። 14 ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤ እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ። 15 “እግዚአብሔር ትክክለኛ ነው፤ እርሱ ዐለቴ ነው፤ በርሱ ዘንድ እንከን የለም” ይላሉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.