1 ተሰሎንቄ 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየጌታ ቀን 1 ወንድሞች ሆይ፤ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ልንጽፍላችሁ አያስፈልግም። 2 ምክንያቱም እንደ ሌባ እንዲሁ የጌታ ቀን በሌሊት እንደሚመጣ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ። 3 ሰዎች፣ “ሰላምና ደኅንነት ነው” ሲሉ፣ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት እንዲሁ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም። 4 እናንተ ግን፣ ወንድሞች ሆይ፤ ይህ ቀን እንደ ሌባ ያስደነግጣችሁ ዘንድ በጨለማ ውስጥ አይደላችሁም፤ 5 ሁላችሁም የብርሃን ልጆች፣ የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ ወገን አይደለንም፤ 6 እንግዲህ እንንቃ፤ ራሳችንንም እንግዛ እንጂ እንደሚያንቀላፉት እንደ ሌሎቹ አንሁን። 7 የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉ፤ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና። 8 እኛ ግን የቀን ሰዎች ስለ ሆንን፣ እምነትንና ፍቅርን እንደ ጥሩር ለብሰን፣ የመዳንን ተስፋ እንደ ራስ ቍር ደፍተን፣ ራሳችንን በመግዛት እንኑር፤ 9 እግዚአብሔር ድነትን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንድናገኝ ነው እንጂ ለቍጣ ወስኖ አላስቀመጠንምና። 10 ብንነቃም ሆነ ብናንቀላፋ ከርሱ ጋራ በሕይወት እንድንኖር እርሱ ስለ እኛ ሞተ። 11 ስለዚህ በርግጥ አሁን እንደምታደርጉት ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ፤ አንዱም ሌላውን ያንጽ። የመጨረሻ ምክር 12 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በእናንተ መካከል በትጋት የሚሠሩትን፣ በጌታም የበላዮቻችሁና መካሪዎቻችሁ የሆኑትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ 13 ስለ ሥራቸውም በፍቅር እጅግ አክብሯቸው። እርስ በርሳችሁም በሰላም ኑሩ። 14 ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እንመክራችኋለን፤ ሥራ ፈቶችን ገሥጿቸው፤ ፈሪዎችን አደፋፍሯቸው፤ ደካሞችን እርዷቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ። 15 ማንም በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁልጊዜ መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ። 16 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ 17 ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ 18 በማናቸውም ሁኔታ አመስግኑ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ይህ ነውና። 19 የመንፈስን እሳት አታዳፍኑ፤ 20 ትንቢትን አትናቁ። 21 ነገር ግን ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ፤ 22 ከማንኛውም ዐይነት ክፉ ነገር ራቁ። 23 የሰላም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና ሥጋችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ያለ ነቀፋ ይጠበቁ። 24 የጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ያደርገዋል። 25 ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ። 26 የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ሁሉ በተቀደሰ አሳሳም ሰላም በሏቸው። 27 ይህ መልእክት ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ ዐደራ እላችኋለሁ። 28 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.