መዝሙር 138 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 138 የዳዊት መዝሙር። 1 በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ “በአማልክት” ፊት በመዝሙር አወድስሃለሁ። 2 ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ ታማኝነትህ፣ ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ፤ ስምህንና ቃልህን፣ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አድርገሃልና። 3 በጠራሁህ ቀን መልስ ሰጠኸኝ፤ ነፍሴን በማደፋፈርም ብርቱ አደረግኸኝ። 4 እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፍህን ቃል በሰሙ ጊዜ፣ የምድር ነገሥታት ሁሉ ያመስግኑህ። 5 የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና፣ ስለ እግዚአብሔር መንገድ ይዘምሩ። 6 እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤ ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል። 7 በመከራ መካከል ብሄድም፣ አንተ ሕይወቴን ትጠብቃታለህ፤ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጅህን ትዘረጋለህ፤ በቀኝ እጅህም ታድነኛለህ። 8 እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያለውን ዐላማ ይፈጽማል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ለዘላለም ነው። የእጅህንም ሥራ ቸል አትበል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.