መዝሙር 147 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 147 1 ሃሌ ሉያ። አምላካችንን በመዝሙር ማወደስ እንዴት መልካም ነው! እርሱን ማመስገን ደስ ያሰኛል፤ ይህ ተገቢም ነው። 2 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን መልሶ ይሠራታል፤ ከእስራኤል የተበተኑትን ይሰበስባል። 3 ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል። 4 የከዋክብትን ብዛት ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል። 5 ጌታችን ታላቅ ነው፤ እጅግ ኀያልም ነው፤ ለጥበቡም ወሰን የለውም። 6 እግዚአብሔር ትሑታንን ከፍ ያደርጋል፤ ክፉዎችን ግን ወደ ምድር ይጥላል። 7 ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ፤ ለአምላካችንም በመሰንቆ ምስጋና አቅርቡ። 8 ሰማይን በደመናት የሚሸፍን እርሱ ነው፤ ለምድርም ዝናብን ይሰጣል፤ በተራሮችም ላይ ሣር ያበቅላል። 9 ለእንስሳት ምግባቸውን፣ የቍራ ጫጩቶችም ሲንጫጩ የሚበሉትን ይሰጣቸዋል። 10 እርሱ በፈረስ ኀይል አይደሰትም፤ በሯጭም ብርታት ላይ ደስታውን አያደርግም። 11 ነገር ግን እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል። 12 ኢየሩሳሌም ሆይ፤ እግዚአብሔርን አመስግኚ፤ ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽን አወድሺ። 13 እርሱ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቷልና፤ ልጆችሽንም በውስጥሽ ባርኳል። 14 በድንበርሽ ውስጥ ሰላም ያሰፍናል፤ ማለፊያ ስንዴም ያጠግብሻል። 15 ትእዛዙን ወደ ምድር ይልካል፤ ቃሉም እጅግ በፍጥነት ይሮጣል። 16 ዐመዳዩን እንደ በርኖስ ይዘረጋል፤ ውርጩን እንደ ዐመድ ይነሰንሳል። 17 የበረዶውን ድንጋይ ቍልቍል ይወረውረዋል፤ በውሽንፍሩስ ቅዝቃዜ ፊት ማን ሊቆም ይችላል? 18 ቃሉን ልኮ ያቀልጣቸዋል፤ ነፋሱን ያነፍሳል፤ ውሆችንም ያፈስሳል። 19 ቃሉን ለያዕቆብ፣ ሥርዐቱንና ፍርዱን ለእስራኤል ይገልጣል። 20 ይህን ለማንኛውም ሌላ ሕዝብ አላደረገም፤ እነርሱም ፍርዱን አላወቁም። ሃሌ ሉያ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.