ኤርምያስ 51:5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል የተሞላች ብትሆንም፥ እስራኤል መበለት አልሆነችም፤ ይሁዳም ከአምላኩ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ አልራቀም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ፊት፣ በበደል የተሞላች ብትሆንም፣ እስራኤልንና ይሁዳን አምላካቸው የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር አልጣላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል ምንም እንኳ የተሞላች ብትሆን፥ እስራኤልም ሆነ ይሁዳ በአምላካቸው በሠራዊት ጌታ ዘንድ አልተተዉም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ምድራቸው በእኔ በእስራኤል ቅዱስ ዘንድ በበደል የተሞላች ብትሆንም እንኳ እኔ የሠራዊት ጌታ አምላካቸው እስራኤልንና ይሁዳን አልረሳኋቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል ምንም እንኳ የተሞላች ብትሆን፥ እስራኤልም ሆነ ይሁዳ በአምላኩ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ዘንድ አልተጣለም። |
ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደምን አፈሰሰ።
ባሪያዎቹ ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፤ ቀለባችንን ይሰጡን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት ከፍ ከፍ ያደርጉ ዘንድ፥ የተፈታውንም ይጠግኑ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ያደርጉልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ሞገስን ሰጠን።
ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ አገልጋዬ ነህና ይህን ዐስብ፤ እኔ ፈጥሬሃለሁ፤ አንተም ባሪያዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ አትርሳኝ።
ባሕርን የማናውጥ፥ ሞገዱም እንዲተምም የማደርግ አማላክሽ እግዚአብሔር እኔ ነኝና፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
እግዚአብሔር፥ “የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፥ “የተተወች ያይደለች የተወደደች ቅድስት ከተማ” ትባያለሽ።
በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለ ምን መታኸን? ፈውስስ ስለ ምን የለንም? ስለ ምን ተስፋ አደረግን? ነገር ግን መልካም ነገር አልተገኘም፤ የፈውስን ጊዜ ተስፋ አደረግን፤ ነገር ግን ድንጋጤ ሆነ።
እንዳንቀላፋ ሰው፥ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኀያል ስለ ምን ትሆናለህ? አንተ ግን አቤቱ! በመካከላችን ነህ፤ ስምህም በእኛ ላይ ተጠርትዋል፤ አትርሳንም።
ምድሬንም በተጠሉ በጣዖቶቻቸው ሬሳዎች አርክሰዋልና፥ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና አስቀድሜ የበደላቸውንና የኀጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ።”
ትተውኛልና፥ ይህንም ስፍራ እንግዳ አድርገውታልና፥ እነርሱና አባቶቻቸውም ለማያውቋቸው ለሌሎች አማልክት ዐጥነዋልና፥ የይሁዳም ነገሥታት ይህን ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተዋልና፥
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኵሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና ሕማምን አበላቸዋለሁ፤ መራራ ውኃንም አጠጣቸዋለሁ።”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰማይ እጅግ ከፍ ቢል፥ የምድርም መሠረት ፈጽሞ ዝቅ ቢል በዚያ ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ፥ የእስራኤልን ዘር ሁሉ እንቃለሁ ይላል እግዚአብሔር።
አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥” ይላል እግዚአብሔር፤ አንተንም ያሳደድሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም አልተውህም።”
በዚያ ወራት በዚያም ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነዚህን በምድር የተረፉትን ይቅር እላቸዋለሁና የእስራኤል በደል ይፈለጋል፤ አይኖርምም፤ የይሁዳም ኀጢአት ይፈለጋል፥ ምንም አይገኝም።
የያዕቆብ ዕድል ፋንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና። እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው። ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን አይተሃልን? በዚህ የሚያደርጉትን ይህን ኀጢአት ያደርጉ ዘንድ ለይሁዳ ቤት ጥቂት ነገር ነውን? ምድሪቱን በኀጢአት ሞልተዋታል፤ ያስቈጡኝም ዘንድ ተመልሰዋል፤ እነሆም ቅርንጫፉን አስረዝመዋል። ይዘባበታሉም።
እርሱም፥ “የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኀጢአት እጅግ በዝቶአል፤ ምድሪቱም በብዙ አሕዛብ እንደ ተመላች ከተማዪቱም እንዲሁ ዓመፅንና ርኵሰትን ተሞልታለች፤ እነርሱም፦ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል፤ እግዚአብሔርም አያይም” ብለዋል።
የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲህም ይሆናል፤ “እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም” ተብሎ በተነገረበት በዚያ ስፍራ የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ።
ዕራቁትዋንም እንድትቆም አደርጋታለሁ፤ እንደ ሕፃንነትዋ ወራት፥ እንደ ተወለደችባት እንደ መጀመሪያዪቱም ቀን አደርጋታለሁ። እንደ ምድረ በዳም አደርጋታለሁ፤ ውኃም እንደሌላት ምድር አደርጋታለሁ፤ በውኃም ጥም እገድላታለሁ።
እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ምሕረት፥ እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚኖሩትን ይወቅሳልና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም።
በዚያ ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ ትንታግ፥ በነዶችም መካከል እንዳለ እንደ ፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፣ በቀኝና በግራ በዙሪያ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይበላሉ፣ ከዚያም ወዲያ ኢየሩሳሌም በስፍራዋ በኢየሩሳሌም ትኖራለች።
በዚያ ቀን እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ይመክትላቸዋል፣ በዚያም ቀን ከእነርሱ መካከል ደካማው እንደ ዳዊት ይሆናል፣ የዳዊትም ቤት በፊታቸው እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ አምላክ ይሆናል።
እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ተቀብሎአችኋልና፥ እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም።