2 ነገሥት 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የምናሴ ዘመነ መንግሥት ( 2ዜ.መ. 33፥1-20 ) 1 ምናሴም በነገሠ ጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ኀምሳ አምስት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሐፍሴባ ነበረ። 2 እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳራቃቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ። 3 አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለበዓል መሠዊያን ሠራ፤ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከለ፤ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ አመለካቸውም። 4 እግዚአብሔርም፥ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ” ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያን ሠራ። 5 በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያን ሠራ። 6 ልጁንም በእሳት ሠዋ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፤ አስማትም አደረገ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ በእግዚአብሔርም ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ፤ ኣስቈጣውም። 7 እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፥ “በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለዓለም አኖራለሁ፤ 8 ያዘዝኋቸውንም ሁሉ ፥ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደገና አላንቀሳቅስም” ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድ የተቀረጸውንም ምስል አቆመ። 9 ነገር ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው። 10 እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት ቃል እንዲህ ሲል ተናገረ፦ 11 “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ከእርሱ በፊት የነበሩ አሞራውያን ከሠሩት ሁሉ ይልቅ ይህን ክፉ ርኵሰት አድርጎአልና፥ ይሁዳንም ደግሞ በጣዖታቱ አስቶአልና፥ 12 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የሚሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹን ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገርን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ። 13 የሰማርያንም ገመድ የአክዓብንም ቤት ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤ የሽቱ ዕቃ እንዲወለወል ኢየሩሳሌምን ወልውዬ በፊቷ እገለብጣታለሁ። 14 የሕዝቡንም ቅሬታ እጥላለሁ፤ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ምርኮና ብዝበዛ ይሆናሉ፤ 15 አባቶቻቸውን ከግብፅ ከአወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ሠርተዋልና፥ አስቈጥተውኝማልና።” 16 ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደምን አፈሰሰ። 17 የምናሴም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ ሁሉ፥ ያደረገውም ኀጢአት፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 18 ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም አጠገብ ባለው በዖዛ አትክልት ቦታ ተቀበረ፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። የአሞጽ ዘመነ መንግሥት ( 2ዜ.መ. 33፥21-25 ) 19 አሞጽም በነገሠ ጊዜ ሃያ ሁለት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዮጥባ ሰው የሐሩስ ልጅ ሚሱላም ነበረች። 20 አባቱ ምናሴም እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ። 21 አባቱም በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ አባቱም ያመለካቸውን ጣዖታት አመለከ፥ ሰገደላቸውም። 22 የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፥ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም። 23 የአሞጽም ብላቴኖች አሴሩበት፤ ንጉሡንም በቤቱ ውስጥ ገደሉት። 24 የሀገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሴሩትን ሁሉ ገደሉ፤ የሀገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። 25 የአሞጽም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 26 በዖዛም የአትክልት ቦታ ባለው መቃብሩ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |