ኤርምያስ 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የተሰበረው ገንቦ ምሳሌ 1 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ሂድ፤ የሸክላ ሠሪ የሠራውን ገምቦ ግዛ፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎችና ከካህናት ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ 2 በከርሲት በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ሂድ፥ በዚያም የምነግርህን ቃል አንብብ፤ እንዲህም በል፦ 3 “የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በዚህ ስፍራ ክፉ ነገርን አመጣለሁ፤ የሰማውም ሰው ሁሉ ይደነግጣል፤ ጆሮዎቹንም ይይዛል። 4 ትተውኛልና፥ ይህንም ስፍራ እንግዳ አድርገውታልና፥ እነርሱና አባቶቻቸውም ለማያውቋቸው ለሌሎች አማልክት ዐጥነዋልና፥ የይሁዳም ነገሥታት ይህን ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተዋልና፥ 5 እኔም ያላዘዝሁትን፥ ያልተናገርሁትንም፥ ወደ ልቤም ያልገባውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ለበዓል ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ የበዓልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠርተዋልና፤ 6 ስለዚህ እነሆ ይህ ስፍራ የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር። 7 በዚህም ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምክር አፈርሳለሁ፤ በጠላቶቻቸው ፊት በጦርና ነፍሳቸውን በሚሹት እጅ እጥላቸዋለሁ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ። 8 ይህችንም ከተማ ለጥፋትና ለማፍዋጫ አደርጋታለሁ፤ በእርስዋም የሚያልፍ ሁሉ ስለ ተደረገባት መቅሠፍት ሁሉ ይደነግጣል፤ ያፍዋጫልም። 9 የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውንም ሥጋ አበላቸዋለሁ፤ ሁሉም እያንዳንዳቸው ጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውን የሚሹት በሚያስጨንቋቸው ጭንቀትና መከበብ የባልንጀሮቻቸውን ሥጋ ይበላሉ። 10 “ገምቦውንም ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፤ 11 እንዲህም ትላቸዋለህ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሸክላ ማድጋ እንደሚሰባበር ደግሞም ይጠገን ዘንድ እንደማይቻል፥ እንዲሁ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እሰብራለሁ፤ የሚቀበሩበትም ስፍራ ሌላ የለምና በቶፌት ይቀበራሉ። 12 እንዲሁ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አደርጋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ይህችንም ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋለሁ፤ አፈርሳታለሁም። 13 የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች እንደ ቶፌት የረከሱ ይሆናሉ፤ እነዚያም በሰገነታቸው ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ ያጠኑባቸው፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያፈሰሱባቸው ቤቶች ሁሉ ይፈርሳሉ።” 14 ኤርምያስም እግዚአብሔር ትንቢት ሊናገር ወደዚያ ልኮት ከነበረው ስፍራ ከቶፌት ተመለሰ፤ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባይ ቆሞ ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ 15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ቃሌን እንዳይሰሙ አንገታቸውን አደንድነዋልና እነሆ በዚች ከተማና በመንደሮችዋ ሁሉ ላይ የተናገርሁባትን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣለሁ።” |