ኢሳይያስ 51 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢየሩሳሌም ዘለዓለማዊ ድኅነት 1 እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ፥ ስሙኝ፤ የተቈረጣችሁበትን ጽኑዕ ዓለት የተቈፈራችሁባትንም ጥልቅ ጕድጓድ ተመልከቱ። 2 ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፤ ባረክሁትም፤ ወደድሁትም፤ አበዛሁትም። 3 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ደስ አሰኝሻለሁ፤ ባድማሽንም ሁሉ ደስ አሰኛለሁ፤ ምድረ በዳሽንም እንደ ዔድን፥ በረሃዎችሽንም እንደ እግዚአብሔር ገነት አደርጋለሁ። ደስታና ተድላ እምነትና የዝማሬ ድምፅ በውስጧ ይገኝባታል። 4 ሕዝቤ ሆይ፥ ስሙኝ፤ ስሙኝ፤ እናንተም ነገሥታት ተግሣጼን አድምጡኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣልና፥ ፍርዴም ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናልና። 5 ጽድቄ ፈጥና ትመጣለች፤ ማዳኔም እንደ ብርሃን ትደርሳለች፤ አሕዛብ በክንዴ ይታመናሉ፤ ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤ በክንዴም ይታመናሉ። 6 ዐይኖቻችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፤ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፤ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፤ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ፤ ማዳኔም ለዘለዓለም ናት፤ ጽድቄም አታልቅም። 7 ፍርድን የምታውቁ፥ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ፤ የሰዎችን ስድብና ማስፈራራት አትፍሩ፤ አትሸነፉም። 8 እንደ ልብስ ፈጥነው ያረጃሉና አይቈዩም፤ ብል እንደ በላውም ይሆናሉ፤ ጽድቄ ግን ለዘለዓለም፥ ማዳኔም ለልጅ ልጅ ይሆናል። 9 ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ የክንድሽንም ኀይል ልበሺ፤ እንደ ቀድሞውም ዘመን እንደ ጥንቱ ትውልድ ተነሺ። 10 ባሕሩን ያደረቅሽ፥ ጥልቁንም ውኃ ያደረቅሽው፥ የዳኑትም ይሻገሩ ዘንድ ጥልቁን ባሕር ጥርጊያ ጎዳና ያደረግሽ አይደለሽምን? 11 እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ ወደ ጽዮንም በደስታና በሐሤት ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ክብር በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፤ ኀዘንና ልቅሶም ይወገዳሉ። 12 እኔ ነኝ፤ የማጽናናሽ እኔ ነኝ፤ አንቺ እንግዲህ ዕወቂ፤ ማንን ፈራሽ? የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ነውን? 13 አንቺ ግን ሰማያትን የፈጠረውን፥ ምድርንም የመሠረታትን ፈጣሪሽን እግዚአብሔርን ረስተሻል፤ ያጠፋሽ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቍጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሻል፤ ይቈጣሽ ዘንድ መክሮአልና፤ አሁን የሚያስጨንቅሽ ቍጣው የት አለ? 14 ከዳንሽ በኋላ እንግዲህ አይኖርምና፥ አይዘገይምምና። 15 ባሕርን የማናውጥ፥ ሞገዱም እንዲተምም የማደርግ አማላክሽ እግዚአብሔር እኔ ነኝና፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። 16 ቃሌን በአፍሽ አደርጋለሁ፤ ሰማይን በዘረጋሁበትና ምድርን በመሠረትሁበት በእጄ ጥላ እጋርድሻለሁ፤ ጽዮንንም አንቺ ሕዝቤ ነሽ እላታለሁ። 17 ከእግዚአብሔር እጅ የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተነሺ፤ ተነሺ፤ ቁሚ፤ የሚያንገደግድሽን የቍጣውን ጽዋ ጠጥተሻልና፥ ጨልጠሽውማልና። 18 ከወለድሻቸው ልጆችሽ ሁሉ የሚያረጋጋሽ አጣሽ፤ ከአሳደግሻቸውም ልጆችሽ ሁሉ እጁን ሰጥቶ የሚያነሣሽ የለም። 19 አሁንም እነዚህ ሁለቱ ይጠብቁሻል፤ ማን ያስተዛዝንሻል? እነርሱም ጥፋትና ውድቀት ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንግዲህ የሚያጽናናሽ ማን ነው? 20 ልጆችሽ ዝለዋል፤ እንደ ጠወለገ ቅጠልም በየመንገዱ ዳር ወድቀዋል፤ በአምላክሽ በእግዚአብሔር ቍጣና ተግሣጽ ተሞልተዋል። 21 ስለዚህም ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ የተዋረድሽ፥ ይህን ስሚ፤ 22 ለወገኑ የሚፈርድ አምላክሽ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ የሚያንገደግድሽን ጽዋ የቍጣዬንም ጽዋ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። 23 ወደ በደሉሽና ወደ አጐሰቈሉሽ ሰዎች እጅ፥ ሰውነትሽንም ዝቅ በዪ፥ ድልድይ አድርገን እንሻገርብሽ ወደሚሏት ሰዎች እጅ እመልሰዋለሁ።” በምድርም ላይ በሆድሽ አስተኙሽ፤ መንገደኞችም ሁሉ ረገጡሽ። |