1 ሳሙኤል 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሳሙኤል የመሰናበቻ ንግግር 1 ሳሙኤልም ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ አለ፥ “የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ። 2 አሁንም እነሆ፥ ንጉሡ በፊታችሁ ይሄዳል፤ እኔም አርጅቻለሁ፤ እንግዲህም አርፋለሁ፤ እነሆም፥ ልጆቼ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊታችሁ ሄድሁ። 3 እነሆኝ፥ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ነጠላ ጫማ እንኳን ቢሆን ከማን እጅ መማለጃ ተቀበልሁ? መስክሩብኝ፤ እኔ እመልስላችኋለሁ።” 4 እነርሱም ሳሙኤልን፥ “ግፍም አላደረግህብንም፤ የቀማኸን የለም፤ አላሠቃየኸንም፤ ከእኛም ከማንም እጅ ምንም አልወሰድህም” አሉት። 5 ሳሙኤልም፥ “በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ ዛሬ በዚህች ቀን እግዚአብሔር ምስክር ነው፤ እርሱ የቀባውም ምስክር ነው” አላቸው፤ እነርሱም፥ “አዎ ምስክር ነው” አሉ። 6 ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ፥ “ሙሴንና አሮንን ያላቀ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ምድር ያወጣ እግዚአብሔር ምስክር ነው። 7 አሁንም ቁሙ፤ በእግዚአብሔርም ፊት እፋረዳችኋለሁ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ያደረገውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሁሉ እነግራችኋለሁ። 8 ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ በገቡ ጊዜ ግብጻውያን አስጨነቁአቸው፤ አባቶቻችሁም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ላከ፤ አባቶቻችሁንም ከግብጽ አውጥተው በዚህ ቦታ አኖሩአቸው። 9 አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ፤ ለአሶር ሠራዊትም አለቃ ለሲሣራ እጅ፥ ለፍልስጥኤማውያንም እጅ፥ ለሞዓብም ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ወጉአቸው፤ 10 እነርሱም፦ እግዚአብሔርን ትተን በዓሊምንና ምስሎቹን በማምለካችን በድለናል፤ አሁንም ከጠላቶቻችን እጅ አድነን፤ እናመልክሃለንም” ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ ። 11 እግዚአብሔርም ይሩበኣልን፥ ባርቅንም፥ ዮፍታሔንም፥ ሳሙኤልንም ላከ፤ በዙሪያችሁም ካሉት ከጠላቶቻችሁ እጅ አዳኑአችሁ፤ ተዘልላችሁም ተቀመጣችሁ። 12 የአሞንም ልጆች ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ሳለ፦ እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ንጉሥ አንግሥልን አላችሁኝ። 13 አሁንም የመረጣችሁትን ንጉሥ እዩ፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ንጉሥ ሰጣችሁ። 14 እግዚአብሔርን ብትፈሩ፥ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል። 15 ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ፥ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር እጅ ትመጣለች። 16 አሁንም ቁሙ፤ እግዚአብሔርም በዐይናችሁ ፊት የሚያደርገውን ይህን ታላቅ ነገር ተመልከቱ። 17 የስንዴ መከር ዛሬ አይደለምን? ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤ እርሱም ነጐድጓድንና ዝናብን ይልካል፤ እናንተም ንጉሥ በመለመናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ያደረጋችሁት ክፋት ታላቅ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ፤ ታያላችሁም።” 18 ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም በዚያ ቀን ነጐድጓድንና ዝናብን ላከ፤ ያንጊዜም ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩአቸው። 19 ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን፥ “ንጉሥ በመለመናችን በኀጢአታችን ሁሉ ላይ ይህን ክፋት ጨምረናልና እንዳንሞት ስለ ባሪያዎችህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አሉት። 20 ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ አላቸው፥ “አትፍሩ፤ በእውነት ይህን ክፋት ሁሉ አደረጋችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። 21 ምንም አይደሉምና የማይረቡትንና የማያድኑአችሁን ለመከተል ከእርሱ ፈቀቅ አትበሉ። 22 እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ተቀብሎአችኋልና፥ እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም። 23 ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አሳያችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይንና እግዚአብሔርን ማገልገልን በመተው እርሱን እበድል ዘንድ እግዚአብሔር ይህን አያድርግብኝ። 24 ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ያደረገላችሁንም ታላቅ ነገር አይታችኋልና በፍጹም ልባችሁ በእውነት አምልኩት፤ 25 ነገር ግን ክፉ ብትሠሩ እናንተም፥ ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ።” |