ኢሳይያስ 62 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ጽድቄ እንደ ብርሃን፥ ማዳኔም እንደሚበራ ፋና እስኪወጣ ድረስ ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም። 2 አሕዛብ ጽድቅሽን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። 3 በእግዚአብሔር እጅ ያማረ አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ። 4 ከእንግዲህ ወዲህ፥ “የተተወች” አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፥ “ውድማ” አትባልም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ብሎታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፥ “ደስታዬ የሚኖርባት” ትባያለሽ፤ ምድርሽም፥ “ባል ያገባች” ትባላለች። 5 ጐልማሳም ከድንግሊቱ ጋር እንደሚኖር፥ እንዲሁ ልጆችሽ ከአንቺ ጋር ይኖራሉ፤ ሙሽራም በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፥ እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል። 6 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ጠባቂዎችሽን በቅጥርሽ ላይ ቀንና ሌሊት አቁሜአለሁ፤ እግዚአብሔርን የሚያስቡ ከቶ ዝም አይሉም፤ 7 ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና፥ በምድርም ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ ዝም አትበሉ። 8 እግዚአብሔር፥ “ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፤” ብሎ በጌትነቱና በክንዱ ኀይል ምሎአል። 9 ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፤ ያከማቹትንም ወይን በመቅደሴ አደባባይ ላይ ይጠጡታል። 10 ሂዱና በበሬ ውስጥ ግቡ፤ ለሕዝቤም መንገድን ጥረጉ፤ ድንጋዮቹንም ከጎዳናው አስወግዱ፤ ለአሕዛብም አላማ ያዙ። 11 እነሆ፥ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል፥ “ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ መድኀኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ አለ በሉአት።” 12 እግዚአብሔር፥ “የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፥ “የተተወች ያይደለች የተወደደች ቅድስት ከተማ” ትባያለሽ። |