1 ነገሥት 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደ ሠራ 1 የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ አራት ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ። 2 ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ። 3 በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደ ፊት ዐሥር ክንድ ነበረ፤ ቤቱንም ሠርቶ ጨረሰ። 4 ለቤቱም በዐይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶችን አደረገ። 5 በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ። 6 የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛውም ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ አረፍቶችን አደረገ። 7 ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ ሲሠሩትም መራጃና መጥረቢያ፥ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም። 8 የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ የሚወጡበት መውጫ ነበረው። 9 ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ የቤቱንም ጠፈር በዝግባ ሳንቃዎች አደረገ። 10 በቤቱም ዙሪያ ሁሉ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆኑ ደርቦችን ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው። 11 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን እንዲህ ሲል መጣ፦ 12 “ስለዚህ ስለምትሠራልኝ ቤት በሥርዐቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስባቸውም ዘንድ ትእዛዞቼን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ። 13 በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም።” 14 ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፤ ፈጸመውም። 15 የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ የውስጡን ግንብ በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት አነጠፈው። 16 ከቤተ መቅደሱ አያይዞ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ሃያውን ክንድ በዝግባ ጠርብ ሠራ፤ ከመቅደሱም ከፍሎ ቅድስተ ቅዱሳኑን አደረገ። 17 በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ። 18 የቤቱንም ውስጥ በተጐበጐበና በፈነዳ አበባ፥ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር። 19 በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ። 20 የቅድስተ ቅዱሳኑም ርዝመት ሃያ ክንድ፥ ስፋቱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ሃያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩም ወርቅ ለበጠው። 21 በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ መሠዊያን ሠራ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። 22 የሠራው ቤት ሁሉ እስከ ተፈጸመ ድረስ ቤቱን ሁሉ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው። 23 በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤልን ሠራ። 24 የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ ዐሥር ክንድ ነበረ። 25 እንደዚሁም ሁለተኛው ኪሩብ ዐሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበሩ። 26 የአንዱ ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበረ፤ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ። 27 ሁለቱም ኪሩቤል በውስጠኛው ቤት መካከል ነበሩ። የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። 28 ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው። 29 በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸ። 30 የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ። 31 ለቅድስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ሳንቃዎችን ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን፥ ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ። 32 ሁለቱንም ሣንቃዎች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸባቸው፤ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልንና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጠ። 33 እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ። 34 ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዙ ከሁለት ሣንቃዎች ተሠራ፤ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዙ ከሁለት ሣንቃዎች ተሠራ። 35 የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው፤ እስከ መድረካቸውም የተያያዙ ነበሩ። 36 የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሣንቃ ሠራው፤ በመቅደሱ ፊት ለፊት ላለው ቤት ወለልም መጋረጃ ሠራ። 37 በአራተኛው ዓመት ከሚያዝያ በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ። 38 በዐሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዐቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባት ዓመትም ሠራው። |