ኤርምያስ 43:12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በግብፅም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል፤ ያቃጥላቸውማል፤ ይማርካቸውማል፤ እረኛም ልብሱን እንደሚቀምል እንዲሁ የግብፅን ሀገር ይቀምላታል፤ ከዚያም በሰላም ይወጣል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እርሱ የግብጽ አማልክት ቤተ ጣዖቶች ላይ እሳት ይለኵሳል፤ ያቃጥላቸዋልም፣ አማልክታቸውንም ማርኮ ይወስዳል። እረኛ ልብሱን እንደሚጐናጸፍ የግብጽን ምድር ተጐናጽፎ ከዚያ በሰላም ይሄዳል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን አነድዳለሁ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ያቃጥላቸዋል ይማርካቸዋልም፤ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፤ ከዚያም ስፍራ በሰላም ይወጣል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በግብጽ የጣዖትን ቤተ መቅደሶች ያቃጥላል፤ ጣዖቶቹን ይማርካል፤ እረኛ ለምዱን እንደሚደርብ ግብጽን በግዛቱ ላይ ደርቦ ምንም ጒዳት ሳይደርስበት በድል አድራጊነት ይወጣል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል ያቃጥላቸውማል ይማርካቸውማል፥ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፥ ከዚያም በሰላም ይወጣል። |
እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ ሀገር አልፋለሁ፤ በግብፅም ሀገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ በቀልን አደርግባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
ስለ ግብፅ የተነገረ ራእይ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፤ የግብፅም የእጆቻቸው ሥራዎች በፊቱ ይዋረዳሉ፤ የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሆነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ” ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ፥ “ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! ጣዖቶችዋም ሁሉ፥ የእጆችዋም ሥራዎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ” አለ።
ቤል ወደቀ፤ ዳጎን ተሰባበረ፤ ምስሎቻቸውም እንደ ትቢያ ሆኑ፤ አራዊትና እንስሳም ይረግጡአቸዋል፤ እንደ ፋንድያም ሸክም የሚያጸይፉ ናቸውና አያነሡአቸውም።
ዐይንሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊአቸዋለሽ ይላል እግዚአብሔር።
ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፤ ጽዮን ሆይ፥ ኀይልሽን ልበሺ፤ አንቺም ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንቺ አያልፍምና ክብርሽን ልበሺ።
በእግዚአብሔርም እጅግ ደስ ይላቸዋል። ነፍሴም በእግዚአብሔር ሐሤት ታደርጋለች። ሽልማትን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማቷም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የደስታንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና።
እናንተም፦ ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ፥ ከሰማይም በታች ፈጽመው ይጥፉ ትሉአቸዋላችሁ።
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ።
በሥራሽና በመዝገብሽ ታምነሻልና አንቺ ደግሞ ትያዢያለሽ፤ ካሞሽም ከካህናቱና ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል።
“ለአሕዛብ ተናገሩ፤ አውሩም፤ ዓላማውንም አንሡ፥ አትደብቁ፦ ባቢሎን ተያዘች፤ ቤል አፈረ፤ ሜሮዳክ ፈራች፤ ምስሎችዋም አፈሩ፤ ጣዖታቷም ደነገጡ፤ በሉ።
በባቢሎንም ላይ እበቀላለሁ፤ የዋጠችውንም ከአፍዋ አስተፋታለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርስዋ አይሰበሰቡም፤ የባቢሎንም ቅጥሮች ይወድቃሉ።
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የግብፅን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፤ ብዛቷንም ይወስዳል፤ ምርኮዋንም ይማርካል፤ ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል።
“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶቹን አጠፋለሁ፤ ምስሎቹንም ከሜምፎስ እሽራለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያም በግብፅ ምድር አለቃ አይሆንም፤ በግብፅ ምድር ላይም ፍርሀትን አደርጋለሁ።
እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርንም አማልክት ሁሉ ያከሳቸዋል፣ በአሕዛብም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በስፍራቸው ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።
እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ መረጣቸው ቅዱሳንና ወዳጆች፥ ምሕረትንና ርኅራኄን፥ ቸርነትንና ትሕትናን፥ የውሀትንና ትዕግሥትን ልበሱት።