ኤርምያስ 43 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ነቢዩ ኤርምያስ ፍርድ እንደሚመጣ ማስጠንቀቁ 1 ለእነርሱ አምላካቸው እግዚአብሔር የላከውን ይህን የአምላካቸውን የጌታን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ መናገርን በፈጸመ ጊዜ፥ 2 የሆሻያ ልጅ ዓዛርያስ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ትዕቢተኞችም ሰዎች ሁሉ ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “ሐሰት ተናግረሃል፤ ጌታ አምላካችን፦ ‘በዚያ ለመቀመጥ ወደ ግብጽ አትግቡ’ ብሎ እንድትናገር አልላከህም፤ 3 ነገር ግን ከለዳውያን እንዲገድሉን ወደ ባቢሎንም ማርከው እንዲወስዱን በእጃቸው አሳልፈህ ልትሰጠን የኔርያ ልጅ ባሮክ በላያችን ላይ አነሣሥቶሃል።” 4 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ የጌታን ድምፅ አልሰሙም። 5 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ ከተሰደዱባቸው ከአሕዛብ ስፍራዎች ሁሉ የተመለሱትን የይሁዳን ትሩፍ ሁሉ፥ 6 ወንዶችንና ሴቶችን ልጆችንም ሕፃናትንም የንጉሡንም ሴቶች ልጆች፥ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከሳፋን ልጅ ከአኪቃም ልጅ ከጎዶልያስ ጋር የተዋቸውን ሰዎች ሁሉ፥ ነቢዩንም ኤርምያስን የኔርያንም ልጅ ባሮክን ወሰዱ፤ 7 የጌታንም ድምፅ አልሰሙምና ወደ ግብጽ ምድር ገቡ፥ እስከ ጣፍናስ ድረስ መጡ። 8 በጣፍናስም የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9 “ትላልቅ ድንጋዮች በእጅህ ውሰድ፥ የይሁዳም ሰዎች እያዩ በጣፍናስ በፈርዖን ቤት መግቢያ ባለው በቅጥራኑና በጡቡ ደጃፍ ሸሽጋቸው፤ 10 እንዲህም በላቸው፦ ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ልኬ ባርያዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን አመጣለሁ፥ ዙፋኑንም እኔ በሸሸግኋቸው በእነዚህ ድንጋዮች ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም የዙፋኑን ድንኳን በላያቸው ይዘረጋል። 11 መጥቶም የግብጽን ምድር ይመታል፥ ለሞትም የሚሆነውን ለሞት፥ ለምርኮም የሚሆነውን ለምርኮ፥ ለሰይፍም የሚሆነውን ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል። 12 በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን አነድዳለሁ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ያቃጥላቸዋል ይማርካቸዋልም፤ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፤ ከዚያም ስፍራ በሰላም ይወጣል። 13 በግብጽም ምድር ያለውን የሄልዮቱን ከተማ ሐውልቶች ይሰብራል፥ የግብጽንም አማልክት ቤቶች በእሳት ያቃጥላል።’ ” |