ኤርምያስ 43 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኤርምያስ ወደ ግብጽ መወሰዱ 1 አምላካቸው እግዚአብሔር እንድነግራቸው ያዘዘኝን ሁሉ ለሕዝቡ ተናግሬ ፈጸምኩ፤ 2 ከዚያ በኋላ የሆሻያ ልጅ ዐዛርያስ፥ የቃሬሐ ልጅ ዮሐናንና ትዕቢተኞች የሆኑ ሌሎችም ሰዎች ሁሉ እንዲህ አሉ፦ “ውሸትህን ነው፤ አምላካችን እግዚአብሔር እኛ ወደ ግብጽ ሄደን እዚያ እንዳንኖር ትነግረን ዘንድ አላከህም፤ 3 ባቢሎናውያን በእኛ ላይ እንዲሠለጥኑብንና ቢፈልጉ እንዲገድሉን ወይም ወደ ባቢሎን ማርከው እንዲወስዱን ያነሣሣ የኔሪያ ልጅ ባሮክ ነው፤” 4 በዚህም ዐይነት ዮሐናንም ሆነ የሠራዊት አለቆች ሁሉ፥ እንዲሁም ከሕዝቡ ወገን ማንም በይሁዳ ምድር ለመኖር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልፈጸሙም፤ 5 ከዚህም በኋላ ዮሐናንና የሠራዊት አለቆች በይሁዳ የተረፉትን በሙሉ ወደ ግብጽ ወሰዱ፤ ይኸውም ከዚህ በፊት በአሕዛብ መካከል ተበታትነው ከቈዩ በኋላ እንደገና ወደ ይሁዳ አገር ተመልሰው የነበሩትን ሕዝብ ማለትም፥ 6 ወንዶችንም ሴቶችንም፥ ሕፃናትንና የንጉሡን ሴቶች ልጆች ጭምር ወሰዱአቸው፤ የባቢሎን ጦር አዛዥ ናቡዛርዳን በገዳልያ ሥልጣን ሥር እንዲጠበቁ የተዋቸውን ሁሉ፥ እንዲሁም እኔንና ባሮክን ወሰዱ። 7 የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጣስ ወደ ግብጽ ሄደው እስከ ጣፍናስ ከተማ ደረሱ። 8 በዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 9 “ጥቂት ታላላቅ ድንጋዮች ፈልገህ ካገኘህ በኋላ ከእስራኤል ልጆች ጥቂቱ እያዩህ በከተማይቱ ቤተ መንግሥት መግቢያ ፊት ለፊት ባለው ከሲሚንቶ በተሠራው ወለል ሥር ቅበረው። 10 ከዚያም የእስራኤል አምላክ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አገልጋዬ የሆነውን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ወደዚህ ስፍራ አምጥቼ አንተ በቀበርካቸው በእነዚያ ድንጋዮች ላይ ዙፋኑን ዘርግቶ የቤተ መንግሥት ድንኳኖቹን የሚተክልባቸው መሆኑን ንገራቸው። 11 ናቡከደነፆር መጥቶ ግብጽን ድል ይነሣል፤ በበሽታ እንዲሞቱ የተወሰነባቸው በበሽታ ይሞታሉ፤ ተማርከው እንዲወሰዱ የተወሰኑ ይማረካሉ፤ በጦርነት እንዲሞቱ የተወሰኑ በጦርነት ይገደላሉ። 12 በግብጽ የጣዖትን ቤተ መቅደሶች ያቃጥላል፤ ጣዖቶቹን ይማርካል፤ እረኛ ለምዱን እንደሚደርብ ግብጽን በግዛቱ ላይ ደርቦ ምንም ጒዳት ሳይደርስበት በድል አድራጊነት ይወጣል። 13 በግብጽ ውስጥ በሄሊዮፖሊስ ከተማ የሚገኙትን ከድንጋይ የተሠሩ ሐውልቶችን ይደመስሳል፤ የግብጻውያንን ጣዖቶችንና ቤተ መቅደሶችን ያቃጥላል።” |